ቀጥታ፡

ወጣቶች በሀገራዊ ልማት ጉልህ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ድጋፍና ክትትል አስፈላጊ ነው

ሀዋሳ፤ ግንቦት 14/ 2017 (ኢዜአ)፡-የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በሀገራዊ ልማት ጉልህ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ድጋፍና ክትትል አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ።

የሲዳማ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ምስረታ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወይዘሮ የሺወርቅ አያና ምክር ቤቱ መመስረቱ ወጣቱ የተስተካከለ ስብዕና እንዲሁም የዳበረ የሥራ ባህል እንዲኖረው ያግዛል። 


 

ለሀገር የልማትና የሰላም እንቅስቃሴ የወጣቱ ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለመረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች ከተጠቃሚነት ባለፈ በሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ጉልህ አሻራቸውን ማሳረፍ እንዲችሉ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉትን ክትትልና ድጋፍ እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴሩ በሀገር ደረጃ እየተከናወነ ላለው የወጣቶች ምክር ቤት አደረጃጀት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ወይዘሮ የሺወርቅ አውስተዋል፡፡

እንደእሳቸው ገለጻ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤትን ከማጠናከር ባሻገር በሰባት ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደር የወጣቶች ምክር ቤት ተመስርቷል።

የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ የክልሉ ወጣቶች በተፈጠሩላቸው የተለያዩ አደረጃጀቶች መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ የአመለካከት ለውጥ እያመጡ ነው። 


 

በዚህም ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ፈጣሪ በመሆን ከራሳቸው ባለፈ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች በማህበራዊ ዘርፍ በተለይ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች የበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጫና ያቃለሉ ተግባራትን ማከናወናቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ምክር ቤቱ ወጣቶች በየዘርፉ በተደራጀ መልኩ የሚያደርጓቸውን ተሳትፎ የማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱም በሠላምና ልማት እንቅስቃሴ ያላቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆኖ የተመረጠው ወጣት ይስሀቅ ሳምቡሬ በበኩሉ እንዳለው፣ ወጣቶች ተደራጅተው በራሳቸው ጉዳይ በነጻነት መምከርና መወሰናቸው ለዘላቂ ሠላምና ልማት አበርክቶው የጎላ ነው።


 

"ምክር ቤቱ ወጣቶችን በማነቃቃት በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ብሎም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ይሰራል" ብሏል፡፡

በክልሉ ዛሬ የተመሰረተው የወጣቶች ምክር ቤት 59 አባላት ያሉት ሲሆን ዘጠኙ የሥራ አስፈፃሚዎች መሆናቸውን ታውቋል።

በምክር ቤቱ ምስረታ መርሀ ግብር ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም