የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርታዊ ውድድር ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርታዊ ውድድር ተጠናቀቀ

አሶሳ፤ግንቦት 14/2017(ኢዜአ):-በባምባሲ ከተማ ለ12 ተከታታይ ቀናት የተካሄደው 6ኛው መላው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርታዊ ጨዋታዎች ውድድር ተጠናቀቀ።
በውድድሩ 16 ወረዳዎች በ11 የስፖርት ዓይነቶች የተሳተፉ ሲሆን አሶሳ ከተማ አስተዳደር ወረዳ አንድ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም መንሱር፥ ውድድሩ ክልሉ በሁሉም ስፖርት አይነቶች አቅም እንዳለው ያሳየበት ነው ብለዋል።
በቀጣይም ለስፖርት ልማት ትኩረት በመስጠት ክልሉ ተተኪ ስፖርተኞችን እንዲያፈራ ይሰራል ብለዋል።
በውድድሩ ክልሉን በሀገር አቀፍ ውድድር የሚወክሉ 128 ስፖርተኞች መመረጣቸውን ገልጸዋል።
በውድድሩ በአትሌቲክስ ስፖርት የተሳተፈችው ደራርቱ መልካሙ ውድድሩ አቅማችን የፈተሽንበት እና በርካታ ተፎካካሪዎች ያየንበት ነው ብላለች።
ሌላው በፓራ ኦሎምፒክ የተሳተፈው መልሰው ለሜሳ፥ ውድድሩ የአካል ጉዳተኞችን በማካተቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግሮ፥ ስፖርት ሁሉንም አካታች መሆን እንዳለበት አመልክቷል።
ውድድሩ በክልሉ ተዘውታሪ ያልሆኑ የስፖርት አይነቶች እንዲታዩ ዕድል ፈጥሯል ያለው ደግሞ ሌላው የውድድሩ ተሳታፊ አብዱሰላም አብድ ነው።
የባምባሲ ከተማ ስፖርተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ ያደረገው ዝግጅት የሚደነቅ መሆኑን ገልጿል።
በተለያዩ የስፖርት አይነቶች አሸናፊ ለሆኑ ተወዳዳሪዎች የዋንጫ እና የሜዳልያ ሽልማት ተሰጥቷል።
በዕለቱም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል አፈጉባኤ አቶ መለሰ ኪዊ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አስር ኢብራሂም፣የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የስፖርት ቤተሰቦች ተገኝተዋል።