ክሮሺያዊው የመሐል ሜዳ ሞተር ሉካ ሞድሪች ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ ሪያል ማድሪድን ሊለቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ክሮሺያዊው የመሐል ሜዳ ሞተር ሉካ ሞድሪች ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ ሪያል ማድሪድን ሊለቅ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14 /2017 (ኢዜአ)፡- የ39 ዓመቱ አንጋፋ ተጫዋች ሉካ ሞድሪች በክረምት ወር ከሚደረገው የዓለም ክለቦች ዓለም ዋንጫ በኋላ ሪያል ማድሪድን እንደሚለቅ አስታወቀ።
ሞድሪች በሳንቲያጎ በርናባው ስታዲየም የመጨረሻ ጨዋታውን የፊታችን ቅዳሜ ቡድኑ ሪያል ሶሲዬዳድን በሚያስተናግድበት የስፔን ላሊጋ የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብር እንደሚያደርግ ስካይ ስፖርትስ ዘግቧል።
ክሮሺያዊው ኮከብ በኢንስታግራም ገጹ ባሰፈረው መልዕክት እንዲመጣ የማልፈልገው ጊዜ መጥቷል፣ ይህ እግር ኳስ ነው ሲል ገልጿል።
በህይወት ሁሉም ነገር መጀመሪያ እና መጨረሻ አለው ሲል ተናግሯል።
ቅዳሜ በበርናባው የመጨረሻ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
ለሪያል ማድሪድ መጫወቴ እንደ እግር ኳስ እና እንደ ግለሰብ ቀይሮኛል ያለው ሞድሪች በክለቡ ስኬታማ እና ወርቃማ ጊዜ ተብሎ ከሚጠቀሱ ዘመኖች መካከል የአንዱ አካል በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል ብሏል።
የሪያል ማድሪድ ክለብን ከልቤ ማመስገን እፈልጋለሁ በተለይም ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ፣ የቡድን አጋሮቼ፣ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎችን አመስግኗል።
በአሜሪካ ከሚካሄደው ከፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ በኋላ በሜዳ ውስጥ የሪያል ማድሪድን ማልያ ባለብስም፤ ሁሌም የማድሪድ ደጋፊ ሆኜ እቀጥላለሁ ሲል ተናግሯል።
የሪያል ማድሪድ ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ሁሌም በሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ይኖራል፤ በክለቡ ያሳረፈው አሻራ ሁሉም ህያው ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸውለታል።
እ.አ.አ በ2012 ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ወደ ሪያል ማድሪድ ያቀናው ሉካ ሞድሪች በሎስ ብላንኮሶቹ በነበረው ቆይታ 6 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ 4 የላሊጋ እና 2 የኮፓ ዴላሬይን ጨምሮ በአጠቃላይ 28 ዋንጫዎችን አንስቷል።
በክለቡ ታሪክ በርካታ ዋንጫ ያነሳ ተጫዋችም ነው።