በመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድር ኮምቦልቻ ከተማ አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድር ኮምቦልቻ ከተማ አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ

ደሴ፤ግንቦት 14/2017( ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ ለተከታታይ 12 ቀናት በተካሄደው የመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድር ኮምቦልቻ ከተማ አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ።
ሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ዞኖች ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
ውድድሩ በእግርና መረብ ኳስ፣ አትሌቲክስ ጨምሮ በ19 የስፖርት አይነቶች ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቂ ኢሳ በማጠናቀቂያ ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለፁት፥ ውድድሩ በክልሉ የተቀዛቀዘውን ስፖርት በማነቃቃት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል ነው።
የተጀረውን መነቃቃት በማስቀጠል ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በማስፋፋትና በማልማት ላይ በማተኮር ይሰራል ብለዋል።
በውድድሩ ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች መሳተፋቸውን ጠቁመው የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር ስለሰላም መስበክ ተችሏል ብለዋል።
ለመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ክልሉን የሚወክሉ ስፖርቶችን መምረጥ መቻሉን ጠቁመው፥ ጨዋታው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፥ ውድድሩ የከተማውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ማነቃቃቱን ጠቁመዋል።
በስፖርታዊ ውድድሮች አንድነትን፣ሰላምንና ልማትን ለማጠናከር የሚደረገው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በውድድሩ ኮምቦልቻ ከተማ በ47 ወርቅ፣ በ29 ብርና በ25 ነሀስ 1ኛ በመሆን አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።
ሰሜን ሸዋ ዞን በ30 ወርቅ፣በ20 ብርና በ18 ነሀስ 2ኛ እንዲሁም ደቡብ ወሎ ዞን በ30 ወርቅ፣ በ19 ብርና በ25 ነሀስ 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
ዛሬ በተካሄደው የማጠቃለያ የእግር ኳስ የፍጻሜ ጨዋታ ሰሜን ወሎ ዞን የእግር ኳስ ቡድን የደሴ ከተማ አቻውን በማሸነፍ ዋንጫ አንስቷል።