በዞኑ የእንሰት ምርት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው-መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የእንሰት ምርት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው-መምሪያው
ሚዛን አማን፣ግንቦት 14/2017(ኢዜአ)፦በሸካ ዞን የእንሰት ምርት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማቅረብና ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ግብርና፣ደን፣አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በአዳዲስ የእንሰት ችግኞች ለመሸፈን መቻሉም ታውቋል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሳለኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ከዞኑ አየር ንብረት ጋር የሚስማሙ ምርጥ የእንሰት ዝርያዎችን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በዞኑ ከ97 በላይ የእንሰት ዝርያዎች እንዳሉ በጥናት መረጋገጡን ገልጸው፥ከእነዚህ ውስጥ በምርታማነታቸው የተሻሻሉ ዝርያዎችን በንቅናቄ የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም ለዘንድሮ ተከላ ከ20 ሚሊዮን በላይ ፈጥነው የሚደርሱ እንዲሁም ድርቅና በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው የእንሰት ችግኝ እየተተከለ መሆኑን ተናግረዋል።
ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በአዲስ የእንሰት ችግኝ መሸፈኑን ጠቅሰው፥ይህም አጠቃላይ የማሳ ሽፋኑን ወደ 40 ሺህ ሄክታር ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
እንሰት በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ባሉ ክፍት ቦታዎችም ጭምር እንዲለማ በንቅናቄ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማሻ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስማማው ታምሩ፥ ዓመታዊ የእንሰት ተከላ ዕቅድ ተይዞ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ባሉ ማሳዎች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ አሰራር ቀደም ሲል እንዳልተለመደ አስታውሰው፥የእንሰት ልማት የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅና በስነምግብ ይዘቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን ያግዛል ብለዋል።
ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በዘንድሮ የበልግ ተከላ ከ50 ሄክታር በላይ ማሳ በእንሰት ችግኝ ለመሸፈን መቻሉንም ጠቅሰዋል።
የማሻ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ አርሶ አደር ደችቶ አድራሮ ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ ያለሙትን እንሰት ለምግብነት ከመጠቀም ባሻገር ቆጮውን በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በግብርና በኩል ቶሎ የሚደርሱና ምርታማ የሆኑ ችግኞች እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ክፍት ቦታዎችን ጭምር በማልማት የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የእንሰት ተክል ልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በመረዳት ስራውን እያሰፋን ነው ያሉት ደግሞ አቶ አሰግድ አሰፋ ናቸው።