በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ ዕድሎች ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ ዕድሎች ትምህርት የሚወሰድባቸው ናቸው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ ዕድሎች ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆናቸውን የ20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለፁ።
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች አህጉራዊ ስብሰባ "የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች የተገኙ ሲሆን ተሳታፊዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ጎብኚዎቹ ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ያሉ የልማት መርሃ ግብሮች አስደናቂና ልምድ የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከካሜሩን የመጡት ፓትሪስ አርሜል ኩንዳ በሰጡት አስተያየት የልማት ሥራዎች ለዜጎች እየፈጠሩ ያሉት የሥራ ዕድሎች ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከደቡብ አፍሪካ የመጡት ዶሮቲ ስቴንካምፕ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የፈጠሩትን የሥራ ዕድል አድንቀው፤ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለው ምቹ ሁኔታ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች አጠቃላይ ገጽታና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን አንስተው፤ በመንግስትና በግል አጋርነት እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችም አስደናቂ ሆነው እንዳገኟቸው ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ለባለሃብቶች በሚያደርጋቸው ማበረታቻዎች መደነቃቸውን የተናገሩት ደግሞ ከታንዛኒያ የመጡት ሊዊቲኮ ምዋንዶቦ ናቸው።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን በተግባር መመልከታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከኢትዮጵያ በርካታ ልምዶች መቅሰማቸውን ነው ጨምረው የገለጹት፡፡