ስራዋን በውጤታማነት በማስቀጠል ለሌሎች ወጣቶችም መትረፍ የቻለችው ወጣት

ብርሃኑ  ፍቃዱ - ከሰቆጣ ኢዜአ 

በ2013 ዓ.ም  የልብስ ስፌት ስራ  የጀመረችው ወጣት ማህደር አስማረ፤ ነዋሪቷ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ  ሰቆጣ ከተማ ነው።

ስራዋን በውጤታማነት የቀጠለችው ወጣት ከአንድ የልብስ ስፌት መኪና ተነስታ ወደ ሶስት የልብስ ስፌት መኪና የደረሰች ሲሆን ካፒታሏንም ከዓመት ዓመት በማሳደግ ላይ ትገኛለች። 

ስራዋን ለመጀመርም  ባጠራቀመችው አነስተኛ ገንዘብ ቤት ተከራይታ ነበር። ከልብስ ስፌት መኪናው በተጨማሪ የሌዘርና የጥልፍ ማሽኖችን በማስመጣት የፋሽንና ዲዛይን ስራና ማሰልጠኛ ማዕከል በመክፈት ለሌሎች ወጣቶች መትረፍ የቻለችበትን አቅም ገንብታለች። 


 

የማሰልጠኛ ማዕከሉን ለመክፈት እስከ 500 ሺህ ብር ወጪ ማድረጓን የገለፀችው ወጣት ማህደር፤ 30 ተማሪዎችን ተቀብላ አጫጭር ስልጠና ለመስጠት የምዝገባና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቃለች። 

"ውጤታማ ለመሆን ጠንክሮ ከመስራት ውጪ ሴትነቴም ሆነ ሌላ ምንም የሚያግደኝ ነገር የለም"  የምትለው ወጣት ማህደር ፤ የፋሽንና ዲዛይን ማሰልጠኛ ማዕከልን ከማስፋት ባለፈ በቀጣይ የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት አቅዳ እየሰራች መሆኑን ገልፃለች።

ወጣት መሰረት ጌታቸው በማህደር የልብስ ስፌትና የፋሽንና ዲዛይን ማሰልጠኛ ማዕከል ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የስራ እድል ተጠቃሚ ሆናለች። 


 

ከድርጅቱ በቂ የልብስ ስፌት ሙያ፣ ልምድና እውቀት መቅሰሟንና  ለዚህም ማህደር እውቀቷንና ልምዷን ሳትሰስት በማከፈሏ  ብቁ ሰራተኛ እንድትሆን አድርጋታለች ።

የማሰልጠኛ ማዕከሉ በከተማዋ መከፈቱ በተለይም ሴቶችና ወጣቶችን በዘርፉ ሰልጥነው የሙያ ባለቤት በመሆን ሰርተው የሚለወጡበት እድል የከፈተ  ነው በማለት ትገልጻለች። 

ከወጣት ማህደር ጊዜን በአግባቡ መጠቀምና ጠንክሮ መስራትንና ቁርጠኝነትን ትምህርት ወስጃለሁ ያለችው ወጣት መሰረት ፤ በልብስ ስፌት ዘርፍ ላይም ውጤታማ ለመሆን እየተጋች መሆኑን ትናግራለች። 

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ሃላፊ ዲያቆን ኪዳነ ማርያም ገብረህይወት፤ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ፀጋ ለይተው ከተንቀሳቀሱ ውጤታማ እንደሚሆኑ ወጣት ማህደር ትልቅ አርአያ ናት ይላሉ። 


 

ለአብነትም  እንደ ወጣት ማህደር ያሉ ታታሪ ወጣቶችን በስፋት ለማፍራት በስራ እድል ፈጠራ ላይ በማተኮር እየተሰራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።

የወጣቷን አርአያነት ለማስፋት  በቀጣይ  የብድር፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታና ሌሎች ድጋፎችን  በማድረግ እንደሚያበረታቱ አረጋግጠዋል።

ወጣቶች  በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል በማድረግ በባለፉት ወራት ለ11 ሺህ ሰዎች  የስራ እድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አውስተዋል።  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም