የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ጠል ፖለቲከኞች ለዘመናት ባራመዱት የመነጠል ትርክት ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር እያሳየ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2017(ኢዜአ)፦ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ጠል ፖለቲከኞች ለዘመናት ባራመዱት የመነጠል ትርክት ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር እያሳየ ነው።

የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች የነበሩት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም የሰሜኑ ግጭት ከተከሰተ በኋላ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር የሰላም ንግግሮች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት ስምምነት እንዳይደረስ እንዲሁም ግጭትና መከፋፈል እንዲቀጥል የሚፈልግ ጥቂት የቀድሞ ህወሃት ቡድን ነበር ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ይህ ቡድን የራሱን የስልጣንና የሀብት ጥቅም ከማጋበስ ያለፈ አላማ እንደሌለው በመግለፅ የትግራይን ህዝብ እንደማይወክልም አንስተዋል።

በግጭቱ ወቅት እኛ ኢትዮጵያ ትውደም እያልን እንኳ በትግራይ አብያተ ክርስቲያናት ጭምር ኢትዮጵያዊነት ይሰበክ ነበር ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን አጽንቶ የኖረ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ለዘመናት ኢትዮጵያ ጠል ሃይሎች ሲነዛ በኖረ የመነጠል ትርክት ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር ማሳየቱንም አንስተዋል።

በግጭቱ ወቅት ህዝቡ ኢትዮጵያን እንዲጠላ ለማድረግ በተሰራጩ የተዛቡ ትርክቶች መጥፎ ስሜቶች መፈጠራቸውን ያነሱት አቶ ጌታቸው፥ ህዝቡ ችግር ሲፈጠርም የሚመጣው ወደ አስመራ ሳይሆን ወደ አዲስ አበባ ነው ብለዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው አንዳንድ አካላት የግልና የንዑስ ቡድን ኩርፊያቸውን የመነጠል ትርክትን በማቀንቀን ለማሳየት ይሞክራሉ ነው ያሉት።

ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ግጭትን በማራዘም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም እንዲደናቀፍ ተደጋጋሚ ሙከራ እንደሚያደርጉ በማንሳት፥ ሆኖም ጸብም ካለ ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከአስተዳደር ጋር መሆን ነበረበት ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ የመነጠል ትርክት በሚያቀነቅኑ አካላት ቅንጣት ታክል የመደናገር ስሜት እንደሌለው በማንሳት፥ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥና በጋራ የመልማት ፍላጎት ነው ያለው ሲሉም ገልጸዋል።

በግጭቱ የተፈጠሩ መጥፎ ስሜቶችን በማረቅ የጋራ እጣፈንታን በአንድነት ለማሳካትም የወል ትርክትን መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ተደራዳሪዎቹ አክለውም፥ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረሙና የሰው ህይወት በመትረፉ የሚቆጫቸው አንዳንድ አካላት አሁንም ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት አላቸው ብለዋል።

ለአብነትም ላለፉት ሁለት ዓመታት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የፌደራል መንግስቱ የጀመራቸውን ሂደቶች እያደናቀፉ በቁስላቸው እየነገዱባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በማስፈጸም በኩል በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ ተጀምሮ ነበር ብለዋል።

ሆኖም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱና በድንኳን እንዲሰቃዩ እያደረገ በቁስላቸው የሚነግደው ሃይል ሂደቱን እያደናቀፈ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ ሃይል የተፈናቃዮች መመለስና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስራውን በአግባቡ መስራት ጥቅሙን ስለሚያስቀርበት አሁንም ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም