ቀጥታ፡

የውይይት ባህል እንዲጎለበት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የጀመረውን ሥራ በማገዝ የድርሻችንን እንወጣለን--የሃይማኖት አባቶች

ሆሳዕና ፤ ግንቦት 13/2017(ኢዜአ):-የውይይት ባህል እንዲጎለበት በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተጀመረውን ጥረት በማገዝ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት አባቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በሆሳዕና ከተማ ትናንት መምከሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡


 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከሲዳማ ክልሎች ከተውጣጡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ጋር ትናንት በሆሳዕና ከተማ መክሯል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች እንደ ሀገር የውይይት ባህል እንዲጎለበት የተጀመሩ ሥራዎች ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ኮሚሽኑ የጀመረውን ስራ እንደሚያግዙ ገልጸዋል።   

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የማዕለላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢ ተወካይና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሀድያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላዕከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እየተለመደ ሊመጣ ይገባል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለልዩነት ምንጭ የሆኑ ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች በውይይት እንዲፈቱና የህብረተሰቡም የውይይት ባህል እንዲዳብር የጀመረው ሥራ ስኬታማ እንዲሆን እንደ ሃይማኖት አባት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። 


 

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ኡስታዝ ሳዲቅ ወጌቦ በበኩላቸው፣ ችግሮችን በውይይት ተነጋግሮ የመፍታት ባህልን ማዳበር ሀገራዊ እድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ ነው።

ሰላም የእስልምና ሀይማኖት ቀዳሚ አስተምህሮ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ ከአስተሳሰብ ጀምሮ ለውይይትና ለሰጥቶ መቀበል የተዘጋጀ አዕምሮ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሰላም እየተጠናከረ እንዲመጣ የሀይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእምነቱ ተከታዮች በሰላም አስፈላጊነት በማስገንዘብ   ለኮሚሽኑ ሥራዎች ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የህብረተሰቡ የውይይት ባህል እንዲጠናከር ኮሚሽኑ የጀመራቸው ሥራዎች ዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮችን በንግግር የመፍታት ልምድን ስለሚያጠናክር ለስኬቱ የበኩላቸውን እንደሚያግዙም ገልጸዋል።     


 

የክልሉ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ሰብሳቢ ወንጌላዊ መስፍን ኢታሞ እንደገለጹት፣ ልዩነቶችን ተወያይቶ በንግግር መፍታት ሰላምን ለማጠናከርና መጨዉን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ያስችላል።  

እንደ ሀይማኖት አባት  ዜጎችን በስነ ምግባር ለማነጽ ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ ኮሚሽኑ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖርና በህብረተሰቡ የውይይት ባህል እንዲዳብር የጀመራቸው ስራዎችን በማገዝ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።  

"ምክክር የጋራ ተግባቦትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማምጣት አይተኬ ሚና አለው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ናቸው።


 

እንደሀገር የውይይት ባህል እንዲጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች ከግብ እንዲደርሱ የባለድርሻ አካላት አስተዋጾ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነት አንጻር የህብረተሰቡ የውይይት ባህል እንዲጎለብት የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።  

ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱን ለማሳለጥ የሚሰራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፣ እስካሁንም የውይይት አጀንዳዎችን በግብዓትነት የማሰባሰብና የህብረተሰብ ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራ ማከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው የምክክር ጉባኤ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝና ዜጎችም የምክክር ባህልን እንዲያዳብሩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም