የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የፀጥታ አካላት በድንበር አካባቢዎች ሰላምን በማጽናትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል በኩል ይበልጥ ተቀራርበው ይሰራሉ

ጋምቤላ፤ ግንቦት 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የፀጥታ አካላት በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች ሰላምን በማጽናትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል በኩል ይበልጥ ተቀራርበው እንደሚሰሩ ገለጹ።

የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ አካላት በድንበር አካባቢ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ በፋጋግ ኩብሪ ቀበሌ ውይይት አካሂደዋል።


 

በውይይቱ በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ዘውዱ በላይ፤ በሁለቱ ሀገራት የድንበር አካባቢዎች ሰላም በማስጠበቅ፣ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል በኩል በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የረጅም ጊዜ አብሮነትና ቤተሰባዊ ግንኙነት ያላቸው ወንድማማች ህዝቦች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይበልጥ እየተጠናከረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም በድንበር አካባቢ የጋራና የተጠናከረ የፀጥታ ቁጥጥር በማድረግ የህዝቡን ሁለንተናዊ ሰላምና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።


 

የደቡብ ሱዳን የመከላከያ ሰራዊት የፓጋግ ኮማንድ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ዋል ዴንግ፣ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ህዝቦች የሰላም፣ የልማት፣ የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በተለይም በድንበር አካባቢ ሰላምን በማፅናት አብሮነትን የማጠናከር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በድንበር አካባቢ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ሰላም የማስጠበቅና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም