በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ83 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍኑ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ83 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍኑ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

አርባምንጭ፤ግንቦት 13/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ83 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍኑ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የደን፣አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፥ በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 83 ሺህ 395 ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።
ችግኞቹ በክልሉ በ12 ዞኖች በመንግስት፣በግለሰብ፣ በማህበራትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በ1 ሺህ 495 የችግኝ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የተዘጋጁት ችግኞች ለአካባቢ ጥበቃ ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።
አሁን ላይ ተከላውን ለማሳካት የሚያግዙ የጉድጓድ ቁፋሮና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ያነሱት አቶ ግዛቴ፥ የአየር ሚዛንን ከማስተካከል ባለፈ የአፈር ለምነትና የውሃ መጠንን በመጨመር ምርትና ምርታማነት እንዲረጋገጥ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ አልፎ ለኢኮ ቱሪዝም መነቃቃት ልዩ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ2011 ዓ/ም የደን ሽፋኑ 17 በመቶ የነበረ ሲሆን በተደረገው ተከታታይ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የደን ሽፋኑ ወደ 23 ነጥብ 17 በመቶ ማደጉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።