የማንችስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ ተጠባቂ የዩሮፓ ሊግጨዋታ 

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 13/2017(ኢዜአ)፡- በ2025 የዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ማንችስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ ዛሬ የሚያደርጉት ፍልሚያ ሁሉም አይኖች አርፈውበታል። 

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ 53 ሺህ ተመልካች በሚያስተናገደው በስፔን ባስክ በሚገኘው ሳን ማሜስ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ በታሪካቸው መጥፎ የሚባል የውድድር ጊዜ ባሳለፉበት “ከክፉ የታሪክ ጠባሳ መዳኛ” ያሉትን ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማሉ።

ማንችስተር ዩናይትድ በሊጉ 39 ነጥብ በመያዝ 16ኛ ደረጃን ይዟል። በውድድር ዓመቱ 21 ሽንፈት አስተናግዷል።

የለንደኑ ክለብ ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሊጉ እስከ አሁን 18 ሽንፈትን አስተናግዶ በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባሳዩት የወረደ ብቃት የሰላ ትችት ያስተናገዱት ሁለቱ ክለቦች የአውሮፓው መድረክ ብቸኛው ጥሩ ነገራቸው ነው ማለት ይቻላል።

ማንችስተር ዩናይትድ በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የፍጻሜ ጨዋታውን የሚያስተናግደው ስታዲየም ባለቤት አትሌቲኮ ቢልባኦን በድምር ውጤት 7 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።

ዩናይትድ በዘንድሮው ዩሮፓ ሊግ ብቸኛው ያልተሸነፈ (በ12 ጨዋታዎች) ክለብ ነው።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በበኩሉ በኖርዌይ ትንሿ ከተማ ቦዶ የሚገኘውን ቦዶ ግሊምትን በደርሶ መልስ  5 ለ 1  በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ ሆኗል። 

ቡድኖች መጥፎ ዓመታቸውን በዋንጫ እና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ለማጠናቀቅ የዛሬው ጨዋታ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው።

የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ለእኔ ትንሹ ችግር ነው፤ ክለቡ ከዛ የጠለቀ ፈተናዎች አሉበት ሲል ተናግሯል።

ዋንጫውን ማንሳት ለደጋፊዎቻችን የምናደርገው ትንሹ ነገር ነው ብሏል።

የቶተንሃም ሆትስፐርሱ አሰልጣኝ አንጌ ፖስቶኮግሉ ዋንጫውን ብናነሳ የዚህ ዓመት መጥፎ የውድድር ዓመታችንን ዞር ብሎ የሚያስታውሰው የለም ነው ያሉት።

ዋንጫው ከክለቡ ቀጣይ ጉዞ ወሳኝ የሚባል ነው ሲልም ገልጿል።

ጉዳት ላይ የነበረው የማንችስተር ዩናይትድ አጥቂ ጆሹዋ ዚርክዜ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ወደ ቢልባኦ መጓዙ ለማንችስተር ዩናይትድ መልካም ዜና ሆኗል።

ዴጃን ኩሉሴቭስኪ፣ ጀምስ ማዲሰን እና ሉካስ ቤርግቫል በጉዳት ምክንያት አለመሰለፋቸው ለለንደኑ ክለብ መጥፎ ዜና ሆኗል። 

የፍጻሜው ጨዋታ አሸናፊ ማንም ይሁን ማንም የሁለቱ ክለቦች የዚህ ዓመት ብቃት ወደፊት በታሪክ መዝገብ አስከፊ በሚል መወሳቱ አይቀሬ ነው።

የ44 ዓመቱ ጀርማናዊ ፍሊክስ ዝዋየር ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም