መንግስት የጤና ባለሙያዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል - ዶክተር ደረጄ ዱጉማ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የጤና ባለሙያዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል - ዶክተር ደረጄ ዱጉማ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 13/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የጤና ባለሙያዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለፁ፡፡
ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በጤና ተቋማት ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም መንግስት የጤና ባለሙያዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ለአብነትም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ስራ የገባው የጤና አስተዳደር አዋጅ የጤና ባለሙያዎችን የዓመታት ጥያቄ በሂደት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በአዋጁ መሰረት የጤና ባለሙያዎች ነፃ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራርንና ተያያዥ ጉዳዮች ወደ ተግባር ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም የጤና ሙያተኛውን በጥቅማ ጥቅምና በሌሎች ሁኔታዎች ሊደግፉ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
በሚኒስቴሩ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የጤና ዘርፍ ሪፎርም ባለሙያውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰፋፊ ጉዳዮች መያዙን ተናግረው፤ ይህንንም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለጤና ባለሙያዎች መግለጽ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተፈጠረው ክስተት በተወሰነ መልኩ የአገልግሎት መስተጓጎል ቢኖርም በሀገሪቱ ባሉ ሁሉም የጤና ተቋማት የሚሰጠው አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡
የጤና ዘርፍ ለአፍታም አገልግሎት መቋረጥ የሌለበት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዓለም ጤና ድርጅት እና በተለያዩ ተቋማት የወጡ ድንጋጌዎች ሰብዓዊነትን በመላበስ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ ህጎችም የጤና ባለሙያ ስራ ማቋረጥ እንዲሁም አድማ ማድረግ እንደሌለበት እንደሚደነግጉም ገልጸዋል፡፡
የህክምና የሙያ ስነ-ምግባርም አገልግሎት ማቋረጥ እንደማይገባ ያስቀምጣል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ባለሙያው ታካሚዎችን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ለማገልገል ቃል መግባቱን ጠቅሰዋል፡፡
ሰሞኑን ከጤና ባለሙያዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች በርካቶች በሞያቸው በገቡት ቃል ኪዳን መሠረት ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ እንደሚገኙም ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ተናግረዋል፡፡