በክረምት የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት አከናውነናል -አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት አከናውነናል -አርሶ አደሮች

ሰቆጣ ፤ግንቦት 13/2017 (ኢዜአ) ፡- በክረምት የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን ከወዲሁ ማከናወናቸውን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የጋዝጊብላና ደሃና ወረዳዎች አርሶ አደሮች ገለጹ።
በመጪው ክረምትም ሊከሰት የሚችል ጎርፍ ለመከላከል ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች 28 ሺህ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ በተራራና በእርሻ መሬት ላይ የእርከን ስራዎች ማከናወን መቻሉን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አመልክቷል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ጋዝጊብላ ወረዳ የዲውና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገናን በዓካል ፤ ባለፈው ክረምት በተከሰተ የጎርፍና መሬት መንሸራተት መኖሪያ ቤታቸውና የእርሻ መሬታቸው ላይ ጉዳት እንዳደረሰባቸው አስታውሰዋል ።
በዘንድሮ ክረምት ተመሳሳይ ክስተት እንዳያጋጥማቸው በበጋው ወቅት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን የጎርፍ ማፋሰሻና የተጠናከረ የተራራ ላይ እርከን መስራታቸውን ተናግረዋል።
በደሃና ወረዳ ብርብራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማሞ ፀጋው በበኩላቸው "ባለፈው ክረምት በአካባቢው ያጋጠመው የጎርፍና መሬት መንሸራተት አደጋ ዘንድሮ እንዳይደገም ህብረተሰቡን ያሳተፈ የእርከን ስራ ሰርተናል" ብለዋል።
"አካባቢያችን ተራራማ በመሆኑ በክረምቱ በመኖሪያ ቤታችንም ሆነ በእርሻችን ላይ ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በበጋው ወቅት አከናውነናል " ያሉት አርሶ አደር ማሞ የተራራ ላይና የእርሻ ውስጥ የእርከን ስራ ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ያከናወኑት የእርከን፣ የውሃ ማፋሰሻ ቦይ ግንባታና ሌሎች ስራዎች ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ከሚያደርስባቸው የቁስና የተዘራ ሰብል ውድመት እንደሚታደጋቸው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።
በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ምህረት መላኩ እንደገለፁት ባለፈው ክረምት በሶስት ወረዳዎች ላይ ባጋጠመው የጎርፍና መሬት መንሸራተት 45 ሽህ ሄክታር መሬት የሸፈነ ሰብል ላይ ጉዳት ደርሷል።
በዚህም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጎጂ መሆናቸውን አስታውሰው ችግሩ በመጭው ክረምትም እንዳይከሰት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች 28 ሽህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በተራራና በእርሻ መሬት ላይ የእርከን ስራዎች መከናወኑን ተናግረዋል።
"በክረምት ወራት የሚያጋጥሙ አደጋዎችን መቀነስ የሚያስችል በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ተከናውኗል" ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ናቸው።
የጎርፍና የመሬት መንሸራተት ተጋላጭነትን ለመቀነስ በተሰሩ የእርከን ስራዎች በክረምት ወራት በስነ- ህይወታዊ ዘዴ የመሸፈን ተግባራት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።