ኢትዮጵያ ለኢጋድ አባል አገራት አስተማማኝ እና ወቅታዊ የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማጋራት ዝግጁ ናት -ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ግንቦት 13/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት አባል አገራት አስተማማኝ እና ወቅታዊ የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ከኢጋድ የስራ ሃላፊዎችና ከኢጋድ አባል አገራት የውሃ ሚኒስቴር ተወካዮች ጋር በተለያዩ የዘርፉ ጉዳች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።


 

በዚሁ ወቅትም በኢጋድ አባል አገራት ድርቅ፣ ጎርፍ እና አውሎ ነፋስ ተደጋግመው የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው ብለዋል።

በነዚህ እና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያትም በሰው፣ በእንስሳት እና በንብረት ላይ ጉዳቶች እንደሚከሰቱ አንስተዋል።

ዛሬ የተደረገው ውይይትም በአባል አገራቱ መካከል የተደራጀ እና የተቀናጀ የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎችን በመለዋወጥ በተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱ ጉዳቶችን ለማስቀረት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል የተተነተነ እና የተደራጀ የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመው፤ ይህን ለማድረግም የአገራት ትብብር እንደሚያስፈልግ ነው የጠቀሱት፡፡

ይህን ትብብር እውን ለማድረግ በአባል አገራቱ መካከል የተደረገው ምክክር አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካሏት የሜቲዎሮሎጂ ጣቢያዎች መካከል 60 በመቶው የሚሆኑት ዘመናዊ ማሽን የተገጠመላቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ያላትን ትልቅ አቅም ለቀጣናው አገራት እያጋራች እንደምትገኝ ገልጸው፣ በቀጣይም አስተማማኝ የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለጎረቤት አገራት ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡


 

በኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከል ኃላፊ አብዲ ፊዳ በበኩላቸው፣ ለአባል አገራቱ የሜትሮሎጂ መረጃዎችን መለዋወጥ አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል የጎላ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ለዚህ የመረጃ ልውውጥ ኢጋድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ተናግረው፤ የኢትዮጵያን የሜቲዎሮሎጂ መረጃ አያያዝን ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች አገራት ለማስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም