ማንችስተር ሲቲ ለሻምፒዮንስ ተሳትፎ ያቀረበውን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ37ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ማንችስተር ሲቲ ቦርንማውዝን 3 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በኢትሃድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኦማር ማርሙሽ፣ በርናርዶ ሲልቫ እና ኒኮ ጎንዛሌዝ የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኦማር ማርሙሽ ከርቀት አክርሮ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ጎል አስደማሚ ነበረች።

ዳንኤል ጄቢሰን ለቦርንማውዝ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ማቴዎ ኮቫቺች ከማንችስተር ሲቲ፣ ሉዊስ ኩክ ከቦርንማውዝ በኩል በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ማንችስተር ሲቲ በ68 ነጥብ ደረጃውን ከ6ኛ ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የተቃረበበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።

ማንችስተር ሲቲ በቀጣዩ እሁድ ከፉልሃም ጋር በሚያደርገው የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ በሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን ያረጋግጣል።

በሊጉ 12ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቦርንማውዝ በ53 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

በማንችስተር ሲቲ 10 ዓመታት ያገለገለው የ33 ዓመቱ ቤልጂየማዊ ኮከብ ኬቨን ደ ብሮይን በኢትሃድ የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጓል።

ለተጫዋቹ የሽኝት መርሃ ግብር በኢትሃድ ተካሄዷል።

ለዘጠኝ ወራት ከጉዳት ርቆ የነበረው የማንችስተር ሲቲው የባለንዶር አሸናፊ ሮድሪ  ወደ ሜዳ ተመልሷል።

በሌላኛው የ37ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ክሪስታል ፓላስ ዎልቭስን 4 ለ 2 አሸንፏል።

ኤዲ ኒኬቲያ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ኤበሬቺ ኤዘ እና ቤን ቺልዌል ቀሪዎቹን ግቦች ለክሪስታል ፓላስ ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኢማኑኤል አግባዱ እና ዮርገንሰን ስትራንድ ላርሰን ለዎልቭስ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ክሪስታል ፓላስ በ52 ነጥብ 12ኛ፣ ዎልቭስ በ41 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የፊታችን እሁድ በሚጠናቀቀው የ2024/25 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፉ ቀሪ ክለቦች እነማን ናቸው? የሚለው ጉዳይ አጓጊ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም