ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የረጅም ጊዜ አጋርነት ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ያላቸውን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አጋርነት የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሶስተኛው የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ ነገ በብራሰልስ ይካሄዳል።

በስብስባው ላይ ለመሳተፍ ብራሰልስ የገቡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲኬላ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ያለፉት አምስት አስርት ዓመታትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አድንቀዋል።

ሁለቱ ወገኖች የጋራ ጥቅሞችን ባከበረ መልኩ ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማትን ለማረጋገጥ በጋራ በቁርጠኝነት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት አጋርነትን የበለጠ ማጠናከር እንዲሁም በሁሉን አቀፍ የስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት ያሉ የጋራ ጉዳዮችን በቁርጠኝነት መተግበር እንደሚገባም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ጌዲዮን(ዶ/ር) በውይይቱ ኢትዮጵያ የንግድ ምቹነትን ለመፍጠር እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎችን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የኢንቨስትመንት ክንፍ በመሆን እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ስትራቴጂካዊ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።

የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲኬላ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እምቅ የኢንቨስትመንት እና የንግድ እድሎች ያሏት ሀገር ናት ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ ቁልፍ ሚና እየተወጣች እንደምትገኝም አመልክተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር በእኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት የአጋርነት መርህ የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በቀጣናዊ ሰላም እና የኢኮኖሚ ልማት ላይ የመከሩ ሲሆን ትብብራቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደሚሰሩ ስለመግለጻቸው ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም