የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን መሰረት ያደረገ የሰው ሀብት ልማት የኢትዮጵያን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን መሰረት ያደረገ የሰው ሀብት ልማት የኢትዮጵያን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን መሰረት ያደረገ የሰው ሀብት ልማት የኢትዮጵያን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የኢራስመስ ፕላስ 2025 ጉባኤ "የትምህርት ሚና ለአረንጓዴ ልማት ሽግግር" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን በተለያዩ የልማት ኢኒሼቲቮች አካታ እየሰራች ትገኛለች።
የታዳሽ ሃይል ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን ዘላቂ የዕድገት ጉዞ ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ከንግግር ባለፈ በተግባር ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደትም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሰው ሀብት ልማት ስራዎችም በዚሁ አቅጣጫ እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።
በሀገሪቱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረት የተቃኘና በክህሎትና በእውቀት የዳበረ የሰው ሀብተ ልማት የኢትዮጵያን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥና የተወዳዳሪነት አቅምን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለአፍሪካ ጭምር አቅም የሚሆን ተግባር እያከናወነች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ይህም ሀገራዊና አህጉራዊ የመጪ ዘመን ርዕይን ለማሳካት ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
የአውሮፓ ሀገራት በኢራስመስ መርሃግብር በኩል ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በአቅም ግንባታና በስልጠና ዘርፍ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ለሰው ሀብት ልማት አጋዥ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ሮቤርቶ ሺሌሮ በበኩላቸው፥ የአውሮፓ ህብረት ለትምህርት ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ጉባኤውም በአውሮፓና አፍሪካ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) የአውሮፓ ህብረት በኢራስመስ መርሃ ግብር በኩል ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ሀገራት ነፃ የትምህርት እድል፣ በትብብር ምርምር መስራትና ሌሎች የፕሮጀክት ድጋፎች እያገኙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ጄይሉ ዑመር (ዶ/ር) የኢራስመስ መርሃግብር ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለማጠናከር አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።