በክልሉ በፍርድ ቤቶች ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎትን ይበልጥ ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በፍርድ ቤቶች ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎትን ይበልጥ ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው
ባህርዳር ፤ ግንቦት 12/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በፍርድ ቤቶች ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎትን ይበልጥ በማጠናከር በየደረጃው ፍትሃዊነትን ለማስፈን የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር በዳኝነት ነፃነትና በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ያለው አንድምታና የሽግግር ፍትህ በኢትዮጵያ በሚል የተዘጋጀ ስልጠና በባህርዳር ከተማ እየተሰጠ ነው።
በስልጠና መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደተናገሩት፤ የዳኝነት ነጻነትንና ተደራሽነትን ለማስፋት ወደ ሪፎርም ተገብቶ እየተሰራ ይገኛል።
በሪፎርሙ የባህላዊ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች አዋጆች ፀድቀው ወደ ተግባር መሸጋገራቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ይህም ቅንጅታዊ አሰራርን በማዳበር ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን ለማስከበር የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
በፍርድ ቤቶች ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎትን በማጠናከር ፍትሃዊነትን ለማስፈን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ስልጠናውም የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ብሎም ልምድ ልውውጥ የሚደረግበት በመሆኑ የነቃ ተሳትፎ እንደሚደረግበት አመልክተዋል ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው፤ ህገ መንግስቱ ለዳኝነት ነፃነት፤ ፍትሃዊነትና ገለልተኝነት መረጋገጥ ዋስትና መስጠቱን ተናግረዋል።
ይህም የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትን በማስፈን የዜጎች እርካታን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ዳኞች የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች በህግ፣ በፍሬ ነገርና በማስረጃ ተመስርተው መስጠት የሚያስችላቸውን የፍትህ ስርዓት ለመገንባት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ይህም ዜጎች በፍርድ ቤቶች ፍትሃዊና ገለልተኝነት ላይ ያላቸው እምነት እንዲፀና እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚቆየው ስልጠና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ዳኞች፤ የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።