ቀጥታ፡

በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡ 41 ቅርሶችን ማስመለስ ተችሏል - ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በቅርስ ጥበቃ በተከናወኑ ጠንካራ ተግባራት በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡ 41 ቅርሶችን ማስመለስ መቻሉን የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ግንቦት 14 እና 15 ቀን 2017 ዓም የሚካሄደውን ሁለተኛ ዙር የቅርስ ምርምር ጉባኤ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሁለተኛው ዙር የቅርስ ምርምር ጉባኤ ''ምርምር ለቅርስ ጥበቃ አና ልማት'' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባኤው አዳዲስ የቅርስ ጥበቃና ልማት ስልቶች የሚተዋወቁበት እንዲሁም ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች የሚዳሰሱበት መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ትብብሮች የሚፈጠሩበትና ለፖሊሲ አውጪዎች ምክረ ሃሳቦች የሚተዋወቁበት እንደሚሆን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በዘርፉ ከተከናወኑት ጠንካራ ተግባራት በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር የወጡ 41 ቅርሶችን ማስመለስ መቻሉንም ተናግረዋል።

ከ30 በላይ ቅርሶች እሴታቸውን ጠብቀው መጠገናቸውንና የቅርስ መረጃዎችን ወደ ዲጂታል አገልግሎት መለወጥ መቻሉን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በቅርስ ምርምር፣ ጥበቃና ልማት ዘርፍ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ነው የጠቀሱት።

የባለስልጣኑ የቅርስ ምርምር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዮናስ ይልማ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ 12 የሚዳሰሱ እና 6 የማይዳሰሱ ቅርሶችን በአለም አቀፍ ደረጃ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ቅርሶችን ከማስመዝገብ አንፃር ባሕላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን የማጥናትና የመለየት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት ቅርሶችን ለማስመዝገብ የተሰራው ስራ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ከጎረቤት ሀገራት ጋር አንድ የሚያደርጉ ቅርሶችን በአለም አቀፍ ደረጃ በጋራ ለማስመዝገብ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እንደተገኘባቸው ገልፀዋል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ሉሲ ወይም ድንቅነሽ የተገኘችበት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል የሚከናወን ሲሆን በእድሳት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓም አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም