ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የምክክር ባህል እንዲጎለብት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

ሆሳዕና፤ ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የምክክር ባህልን በማጎልበት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚሰራው ሥራ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

ኮሚሽኑ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያና ከሲዳማ ክልሎች ከተውጣጡና ከተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በሆሳዕና ከተማ እየመከረ ነው።


 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት በሀገሪቷ ዘላቂ ሰላምንና እድገት ለማረጋገጥ የምክክር ባህልን ማሳዳግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ሰላምን በማጠናከር በሀገሪቷ ለሚስተዋሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የምክክር ባህልን ለማጎልበት በሚሰራው ሥራ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የምክክር ሂደት ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው፣ በዚህም የጋራ ተግባቦት መፍጠር የሚቻልበት ምህዳር እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬው መድረክም እንደ ሀገር በኮሚሽኑ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማስመልከት ለባለድርሻ አካላት ግልጽነት መፍጠርን ዓላማ ማድረጉን አስረድተዋል።

እንደ ሀገር ምክክርን ባህል በማድረግ ዘላቂ ሰላምና እድገት ለማስመዝገብ የተጀመረውን ጥረት እውን ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ለአብሮነትና ሰላም መጠበቅ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ያላቸው ሚና የማይተካ መሆኑንም ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ሊህቃን ያላቸው ሚና እንዲሁም በኮሚሽኑ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አፈፃፀምን የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትም አመልክተዋል፡፡ 

በመርሃ ግብሩ ላይ ከሦስቱም ክልሎች የተውጣጡ የባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም