የኢጋድ አባል ሀገራት አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ለማመንጨት ጠንካራ ስርዓት መዘርጋት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ አባል ሀገራት አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ለማመንጨት ጠንካራ ስርዓት መዘርጋት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ የኢጋድ አባል ሀገራት አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ማመንጨት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባቸው የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር 70ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ምልከታ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአፍሪካ ቀንድ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅና ጎርፍ በርካቶችን እየፈተነ ነው።
ግብርና፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የውሃ ሀብት፣ ቱሪዝምና ጤና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከሚደርስባቸው ዘርፎች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ አስተማማኝና ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃን መተንተንና ማሰራጨት የሚያስችል የተቋም ማዘመንና ጠንካራ ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢጋድ የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል ወቅታዊና አስተማማኝ የአየር ጠባይ መረጃ በማቅረብ የአባል ሀገራቱ የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም ለማጎልበት የሚሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
በየሀገራቱና በአጠቃላይ በቀጣናው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛና አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ማመንጨት የሚያስችሉ ስርዓቶችን ለመዘርጋት ኢንቨስት ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሀመድ አብዲ ዋሬ በበኩላቸው በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ የተለያዩ አደጋዎችና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
ኢጋድ በአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል በኩል ለቀጣናው የአየር ንብረት ትንበያ መረጃን ተደራሽ እያደረገ እንዲሁም ለሀገራቱ ድጋፍ እየሰጠ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፥ መንግስት ኢንስቲትዩቱንና የክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላትን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።
የሙያተኞችን አቅም ለማሳደግና ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጂ ምልከታ ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ከመጪው ሰኔ እስከ መስከረም ባለው ወቅት ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚጠበቅ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ የተናገሩት የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከል የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ ትጥቄ ካሳ(ዶ/ር) ናቸው።
በክረምቱ ወቅት ከመደበኛ በላይ የሚጠበቀው ዝናብ ለግብርና እንቅስቃሴ አስፈላጊ በመሆኑ መንግስታት ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የዝናቡ ሁኔታ የጎርፍና መሰል አደጋዎችን እንዳያስከትልም መረጃን በማጠናከር ቅድመ ጥንቅቄ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።