ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታንዛኒያ የሚያደርገው በረራ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር በማጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታንዛኒያ ከተሞች በሳምንት 49 ጊዜ የሚያደርገው የቀጥታ በረራ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር በማጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ገለጹ።

አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮ-ታንዛኒያ መካከል ከ60 ዓመታት በላይ የተሻገረ ወዳጅነት ተገንብቷል።

የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ፓን አፍሪካኒዝምን በመትከል ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

አሁን ላይ የኢትዮ-ታንዛኒያ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረክ ትብብር አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እ.አ.አ መጋቢት 2024 በታንዛኒያ የኢትዮ-ታንዛኒያን ሁሉ አቀፍ ትብብር ማጠናከር የሚያስችል ስኬታማ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮ-ታንዛኒያ የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባም በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በአቪዬሽን፣ በስደት መከላከልና ሌሎች ዘርፎች ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም በየሁለት ዓመቱ የሀገራቱ የጋራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባን በማካሄድ ስትራቴጂካዊ ትብብራቸውን የሚያጠናክር ግንኙነት መፈጠሩን ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም እንደሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያና ታንዛኒያን በኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በሌላ መልኩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዳሬ ሰላም፣ ዛንዚባርና ኪሊማንጃሮ ከተሞች በሳምንት 49 በረራዎችን በማድረግ ለሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

በታንዛኒያ ከተሞች የሚያደርገው በረራም ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን በማጓጓዝ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ልማት ጉልህ ሚና በመጫወት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እያጠናከረ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናዊና የአህጉራዊ የኢኮኖሚ ነፃነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኤሌክትሪክ አቅርቦት ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ግንባር ቀደም ሚና እየተወጣች መሆኗንም አስታውቀዋል።

በታንዛኒያ በሚካሄዱ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮችም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ማስገንዘብ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በዚህም በሰላምና ደኅንነት፣ በግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ውክልና እንዲሁም መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር ላይ በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ታንዛኒያ የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ተቀብላ ማጽደቋም ሀገራቱ በድንበር ተሻጋሪ ሃብቶች ላይ በትብብር የሚሰሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ እንደሆነ አስረድተዋል።

በቀጣይም የኢትዮ-ታንዛኒያን ሁሉ አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለማጠናከር የባህልና የህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ የንግድና ኢንቨስትመንት በማህበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትብብርን ለማጠናከር እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም