ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የብዝኃ ህይወት ሀብቶቿን ጠብቃ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራች ነው - የብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የብዝኃ ህይወት ሀብቶቿን ጠብቃ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራች ነው - የብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የብዝኃ ሕይወት ሀብቶቿን ጠብቃ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችሉ አሰራሮችን እየተገበረች እንደምትገኝ የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ(ዶ/ር) ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ቀን ለ24ኛ ጊዜ “ከተፈጥሮ ጋር መስማማት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ከግንቦት 12 እስከ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይከበራል።
የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ(ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ብዝኃ ህይወት ለስነ ምህዳር ሚዛን መጠበቅ፣ ለምግብ ስርዓት ዘላቂነት እና ለሰው ልጆች ደህንነት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የብዝኃ ህይወት ጥበቃና አጠቃቀምን በማጎልበት ሀገር በቀል ዝርያዎች እንዳይጠፉ መጠበቅ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የብዝኃ ህይወት ሃብቶቿን ጥበቃ እያጎለበተች መሆኑን ጠቁመው ሀገር በቀል ዝርያዎች እንዳይጠፉ የሚያስችል ሥርዓት ተግባራዊ እያደረገች መሆኗም አንስተዋል፡፡
በብዝኃ ህይወት ያላት ዕምቅ ሃብት መጠበቅና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ድርሻ ርብርብ እንደሚጠይቅ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የዘንድሮው የብዝኃ ህይወት ቀን የዘርፉን ሀብት ጥበቃ ማጎልበት በሚያስችሉ የፓናል ውይይቶች፣ አውደ ርዕይ፣ የመስክ ጉብኝትና ሀገር በቀል ችግኞችን በመትከል ይከበራል ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዮት ብርሃኑ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የብዝሀ ህይወት ስምምነት ፈርመው ከተቀበሉ 196 ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ የፀደቀበትን ዕለት ለማስታወስ ሲባል ግንቦት 14 ዓለም አቀፍ የብዝኃ ሕይወት ቀን ተብሎ መወሰኑን ጠቁመው፤ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.እ.አ ከ2002 ጀምሮ በየዓመቱ በድምቀት እየተገበረ ይገኛል ብለዋል፡፡