በአፍሪካ ድህነትንና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የተግባር ቁርጠኝነትንና ትብብርን ማጠናከር ይገባል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ድህነትንና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የተግባር ቁርጠኝነትንና ትብብርን ማጠናከር ይገባል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ድህነትንና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የሀገራት የተግባር ቁርጠኝነትንና ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች አህጉራዊ ስብሰባ "የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ መርኃ ግብሩ እንደገለጹት፤ ስብሰባው አፍሪካውያን ፖሊሲ አውጪዎችና ባለሙያዎች ፈጠራን መሰረት ያደረገ ስራ ለመፍጠር፣ ድህነትን ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚያግዝ ነው፡፡
ይሄንን ለማሳካት ደግሞ በአህጉሪቱ የሁሉንም የጋራ ጥረት ይጠይቃል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ጥረት እንዲሁም ብሔራዊ የድርጊት መርሀ ግብር ለንግድ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
ፖሊሲዎች፣ የልማት ስትራቴጂዎች እንዲሁም የመሰረተ ልማት ሀብቶች ለስራ እድል ፈጠራና ለአካታች ለውጥ መሰረት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የልማት ግቦቻችን ለሥራ ፈጠራ ትኩረት የሚሰጡ ናቸው ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ድህነትን ለመቀነስ፣ የሥራ እድል ለመፍጠርና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ስብሰባ የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት የጋራ መፍትሔ የማስቀመጥ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ያሉባትን ፈተናዎችና ያሏትን መልካም እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም በትብብር ላይ የተመሰረተ የተግባር ድርጊት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አፍሪካን ከድህነት ኋላ ቀርነትና ከስራ አጥነት የጸዳች ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ትብብርና የጋራ ቁርጠኝነት ይጠይቃልም ነው ያሉት አፈ ጉባኤው በንግግራቸው፡፡