በጋምቤላ ከተማ ከ14 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ጋምቤላ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ከተማ ከ14 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ፕሮጀክት ዛሬ  ይፋ ተደርጓል።

በከተማው የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ለሚደረገው ጥረት የአጋር አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባም ተጠቁሟል። 

የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሳይመን ሙን (ዶ/ር) በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው እንዳሉት መንግስት የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። 


 

በተለይም ደረቅ ቆሻሻን በመሰብሰብና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመሩ ስራዎች ለወጣቱ የስራ እድል በመፍጠር ረገድም አዎንታዊ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም ያገለገሉ ፕላስቲኮችና ደረቅ ቆሻሻዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ከማዋል ባለፈ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። 

የፕላስቲክ ቆሻሻ ለረጅም ዓመታት ሳይበሰብስ በመቆየት አፈርን በኬሚካል የመበከል አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ በጋምቤላ ከተማ ተግባራዊ መደረጉ ችግሩን የሚያቃልል ነው ብለዋል። 

ማህበረሰቡም የፕላስቲክ ምርቶችን ተጠቅሞ ሲያስወግድ አካባቢን በማይበክል መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው  የከተማ አስተዳደሩም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል ። 

ፕሮጀክቱ ደረቅና የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን ሰብስቦ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሰራል ያሉት ደግሞ የኖርዌይ ቤተክርስቲያን እርዳታ ድርጅት የጋምቤላ ክልል አስተባባሪ አቶ በቃሉ ዳኜ ናቸው። 


 

ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሁለት ዓመታት የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በአካባቢ ማስዋብና በቆሻሻ ማስወገድ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ማህበራትና ወጣቶችን በማቀፍ የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል። 

በፕሮጀክቱ ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ከወዳደቁ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የፈጠራ ስራዎችም ቀርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም