ቀጥታ፡

በማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ደህንነትን መሰረት ያደረጉ ሊሆን ይገባል


ቦንጋ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ በማዕድን እና ሌሎች ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ደህንነትን መሰረት ያደረጉ ሊሆን እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ በማዕድን ልማት የተሰማሩ ማህበራትና ድርጅቶች የአካባቢ ጥበቃና የማህበራዊ ደህንነት ህግ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር አድርገዋል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ አስራት ገብረማሪያም (ዶ/ር ኢ/ር)፤ በክልሉ ገና መልማት የሚችል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት መኖሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአካባቢ ጥበቃና የማህበራዊ ደህንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ሃብቶችን በማልማት ለሀገር ጥቅም በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።




በመንግስት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በርካታ ማህበራትና ባለሃብቶች በዘርፉ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የክልሉን እምቅ ሃብት ለማልማት በሚደረገው ጥረት በማገዝ፣ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ረገድ የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ከማዕድን ማምረት ጋር በአካባቢ ላይ ተፅእኖ ሊያደርሱ የሚችሉ አዝማሚያዎች መታየታቸውን ጠቅሰው ችግሩን መከላከልና ዘላቂ መፍትሄ መሻትም ያስፈልጋል ብለዋል።




የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ በመንከባከብና በማልማት ጭምር ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን ነው ያሉት።

የማዕድን ሃብትን ጨምሮ በሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎች የተፈጥሮ ሃብት ጥፋት በማያስከትልና አካባቢን በማይጎዳ መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ስራዎችን በማጠናከር ዘርፉን የሚቀላቀሉ አልሚዎች በዚሁ መሰረት እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም