ቀጥታ፡

ኢጋድ የስደተኞች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ፤ግንቦት 11/2017 (ኢዜአ)፡- የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በቀጣናው የስደተኞች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

ኢጋድ በስደት፣ መፈናቀል እና ከተሜነት ላይ ያዘጋጀው አራተኛው ሳይንሳዊ ኮንፍረንስ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ኮንፈረንሱ የሚከናወነው “ስደት፣ መፈናቀል እና ከተሜነት በዘላቂ ልማት ላይ ያላቸው ተጽእኖ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።


 

ኢጋድ ሁነቱን ያዘጋጀው ከጀርመን የተራድኦ ድርጅት (ጂአይዜድ)፣ የስዊድን መንግስት፣ ዓለም አቀፍ የከተሞች ጥምረት፣ “ReDSS” የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጥምረት እና የኢጋድ ዩኒቨርስቲዎች ፎረም ጋር በመሆን ነው።

በኮንፈረንሱ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በመወከል ንግግር ያደረጉት የኢጋድ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ አበባው ቢሆነኝ በቀጣናው የዜጎች እንቅስቃሴ መጨመር እና የከተማ እድገት ይዟቸው የመጧቸው ፈተናዎች የተቀናጀ እና መረጃን መሰረት ያደረገ ምላሽ እንደሚያሻቸው ገልጸዋል።

ዜጎች በኢጋድ ቀጣና የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በከተሞች እድገት፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ጫና እያሳደሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት፣የስነ ሕዝብ አወቃቀር ለውጦች እና የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊነት ለስደት እና መፈናቀል መሰረታዊ መንስኤዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በቀጣናው የሚገኙ ሀገራት ያሉ ከተሞች እያደጉ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ አበባው፥ ለዚህም ዘላቂ መሰረተ ልማት፣ ሁሉን አቀፍ ፖሊሲዎች እና የአገልግሎት ተደራሽነት ማሳደግ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

ኢጋድ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን እንዲረጋገጥ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት አባል ሀገራቱ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች በፖሊሲ ቀረጻ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እያደረጉት ያለውን ጥረት እየደገፈ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

በኮንፍረንሱ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ስደት፣ መፈናቀል እና ከተሜነት ያላቸውን የተወሳሰበ ትስስር በጥናት በመለየት ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ የመፍትሄ ሀሳቦችን እንዲያፍልቁ ጥሪ አቅርበዋል።

የልማት አጋሮችም በኢጋድ ቀጣና ስደት እና የከተሞች እድገትን አስመልክቶ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ኮንፈረንሱ በኢጋድ ቀጣና ስደት፣ መፈናቀል እና ከተሜነት ያላቸው ውስብስብ ትስስር እና በዘላቂ ልማት ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ላይ በዋናነት ይመክራል።

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቀጣና እና በሀገር ደረጃ ለፖሊሲ የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢጋድ ለስደተኞች እና ተፈናቃዮች ደህንነት እንዲጠበቅ በፖሊሲ ልማት፣ በመሰረተ ልማት እና መብታቸው እንዲከበር የሚያስችሉ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ቀጣናዊ ተቋሙ ለተሰደዱ ዜጎች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እና የሰፈራ ቦታዎች ግንባታ፣የስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የማህበራዊ አገልግሎት እና ማህበራዊ ዋስትና እንዲያገኙ እንዲሁም በሕግ ማዕቀፍ መብታቸው እንዲከበር እየሰራ ይገኛል።

ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ለስደተኞች እና ተፈናቃዮች የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

ሳይንሳዊ ኮንፍረንሱ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም