ሊቨርፑል ከብራይተን ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፡- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ37 ሳምንት መርሃ ግብር የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ከብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን ጋር ይጫወታል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በአሜክስ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሊቨርፑል በ83 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን በ55 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል። 

የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋገጠው ሊቨርፑል እና በአውሮፓ መድረክ የመሳተፍ እድል የሌለው ብራይተን የሚያደርጉት ጨዋታ ለክለቦቹ መርሃ ግብር ከማሟላት የዘለለ ትርጉም የለውም።  

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ ሊቨርፑል 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የ41 ዓመቱ አንዲ ማድሊ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም