ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን መሰረተ ልማት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን መሰረተ ልማት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን መሰረተ ልማት የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት የሚያሻሽል ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች ሌበር ቤዝድ ፕራክቲሽነርስ አህጉራዊ ስብሰባ "የማይበገር ማህበረሰብ እና ጤናማ አካባቢ፦ የሰው ኃይልን በብዛት የሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም አካሄዶች" በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በመርሀ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራና ስራ ስምሪት ለአካታችና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ማህበራዊ ፍትህ መሰረት መሆናቸውን ይገነዘባል።
ስብሰባው የሥራ እድል ፈጠራን፣ ድህነት ቅነሳንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሀሳቦችን በማፍለቅ የጋራ አንድነት እና ቁርጠኝነት የምናሳይበት ነው ብለዋል።
ዓለም በውስብስብ ፈተናዎች ላይ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በአሁኑ ወቅት ለስራ ፈጠራ ችግር ከሆኑት መካከል የአየር ንብረት ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ልዩነት፣ ጂኦ ፖለቲካዊ ግጭት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ ሀገራት ሥራ አጥነትና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት መሆናቸውን ጠቁመው፤ ፈጠራና የተግባር እርምጃ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በቅርበት እንደምትሰራ ገልጸው፤ መንግስት ለሥራ ፈጠራ፣ ለዘላቂ ልማት፣ የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተለይም በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ከስራ እድል ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ግቦችን ለማሳካት በመንግስታት፣ በትምህርት ተቋማት እና በግሉ ዘርፍ መካከል ትብብር መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማትና በሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ስለምትገኝ ተሳታፊዎች ልምድ የሚቀስሙበት መሆኑን ገልጸዋል።
19ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት አህጉራዊ ስብሰባ እኤአ በ2023 "ለጋራ ነጋችን የሥራ ክህሎትና ምርታማነት ማሳደግ" በሚል መሪ ሀሳብ በሩዋንዳ ኪጋሊ መካሄዱን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ 20ኛውን እንድታዘጋጅ የተመረጠችበት እንደነበርም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተሰጣትን ሀላፊነት በመቀበል ስብሰባው ግቡን እንዲመታ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ገልጸው፣ ከስበሰባው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፖሊሲ ስትራቴጂና ፕሮግራም ግብዓት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።