አርሰናል ኒውካስትል ዩናይትድን በማሸነፍ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን አረጋገጠ - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ኒውካስትል ዩናይትድን በማሸነፍ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎውን አረጋገጠ

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 10/2017 (ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ አርሰናል ኒውካስትል ዩናይትድን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዴክላን ራይስ በ55ኛው ደቂቃ የማሸነፊያዋን ጎል አስቆጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ነጥቡን ወደ 71 ነጥብ ከፍ አድርጓል። መድፈኞቹ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።
በ66 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኒውካስትል ዩናይትድ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመሳተፍ የመጨረሻ ሳምንቱን ጨዋታ አሸንፎ የሌሎችን ክለቦች ውጤት ይጠብቃል።
በሌሎች የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሌላኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ተፎካካሪ ኖቲንግሃም ፎረስት ዌስትሃም ዩናይትድን 2 ለ 1 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል። ነጥቡንም ወደ 65 ከፍ በማድረግ 7ኛ ደረጃን ይዟል።
ኤቨርተን ሳውዝሃምፕተንን እና ሌይስተር ሲቲ ኢፕስዊች ታውንን በተመሳሳይ 2 ለ 0 ሲያሸንፉ ፋልሃም ብሬንትፎርድን 3 ለ 2 ረቷል።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እንግሊዝን ወክለው የሚሳተፉ ቀሪ ክለቦች በቀጣዩ ሳምንት በሚደረጉ የ38ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይለያሉ።