ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ ዓለምአቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማዘጋጀት እቅም እያደገ መጥቷል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 10/2017 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማዘጋጀት እቅም እያደገ መምጣቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ዓለም ዓቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖን(ETEX 2025) ጎብኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት፤ ከተማዋ ከአገር አልፎ የዓለም አቀፍ እና አህጉረ አቀፍ ኮንፈረንስ የማዘጋጀት አቅም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በመዲናዋ እየተካሄዱ የሚገኙ ኮንፈረንሶች የከተማዋን ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመው፤ የኮንፈረንስ እና የቱሪዝም መዳረሻነቷን ከማሳደግ በላይ በርካታ የሥራ እድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። 

ባለፉት አስር ቀናት ብቻ በርካታ ኮንፈረንስ እና ኤክስፖዎች መካሄዳቸውን ገልፀው፤ ይህም የከተማዋን ገቢ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በአገሪቷ በቴክኖሎጂ ልማት ከፍተኛ ለውጥ እና እድገት እየተመዘገቡ ይገኛሉም ብለዋል።

መዲናዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

ኤክስፖው ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ የተያዘው ግብ ለማሳካት ጫፍ ላይ ስለመድረሳችን አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ሃይል ለማፍራትና የተፈጠረው አቅም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሳለጥ በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ ሁሉን አቀፍ የተሟላ የኮሪደር ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አውስተው፤ ከተማዋን የማዘመንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የመዘርጋት ስራዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም