ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማጠናከር የበለጠ እንሰራለን - የባህርዳር ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን ለማጽናትና ልማትን ለማጠናከር የበለጠ እንሰራለን - የባህርዳር ወጣቶች

ባህር ዳር፣ ግንቦት 10/2017 (ኢዜአ) ፡-በባህር ዳር ከተማ ሰላምን ለማጽናት፣ የኮሪደርና ሌሎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ወጣቶች ገለጹ።
የከተማው አስተዳደር በሰላምና ልማት ስራዎች ዙሪያ ከከተማው ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ከተሳተፉ የከተማው ወጣቶች መካከል አራጋው ስማቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ አሁን ላይ የተሻለ ሰላም በመስፈኑ አበረታች ለውጥ መመዝገቡን ተናግሯል።
አሁን ለተገኘው ሰላም የወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁሞ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
አሁን ላይ በተሰሩ የሰላም ማስክበር ስራዎች ከተማ አስተዳደሩ የተሻለ ሰላም በማስፈን የኮሪደርና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የተናገረው ደግሞ ወጣት ፀጋየ ደረሰ ነው።
በከተማው የሰላም ማጽናትና ሌሎች የልማት ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቋል።
በከተማው ሰላምን ለማስፈን በተቀናጀ መንገድ በተሰራ ስራ አሁን ላይ ለውጥ መኖሩን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ክቤ የኋላ ናት።
በከተማው የተሰሩ የልማት ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሳ፤ "አሁንም ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሰላሙን በማጽናት በኩል የበኩላችንን እናግዛለን" ብላለች ።
"ሁላችንም ለሰላም ዘብ መቆም ያስፈልገናል" ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ወጣት አበባ መልካሙ ናት።
አመራሩ፣ ወጣቱና የፀጥታ ሃይሉ በሰራው ስራ አሁን ላይ የተሻለ ሰላም ማስፈን እንደተቻለ አንስታ፤ አሁንም ለከተማው ሰላም ለመስራት መዘጋጀቷን አስታውቃለች።
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የከንቲባው የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ግዛቸው በበኩላቸው፤ በከተማው መላ ህዝቡን በማሳተፍ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ተጣምሮ እየተሰራ ነው።
በከተማው የሚደነቅ ልማት መከናወኑን አንስተው፤ በተለይም የኮሪደር ልማቱና ሌሎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀዋል።
በከተማው ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ሰላምን በዘላቂነት ከመገንባት ጎን ለጎን የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ ናቸው" ብለዋል።
በመድረኩ በከተማው ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።