በዞኑ በተፋሰስ ልማት ባገገሙ አካባቢዎች ባከናወነው የልማት ስራ ተጠቃሚ ሆነናል - አርሶ አደሮች

ወልቂጤ፤ ግንቦት 10/2017 (ኢዜአ) ፡-በጉራጌ ዞን በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መልሰው እንዲያገግሙ በተደረጉ አካባቢዎች እያከናወኑ ባሉት የልማት ስራ ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ አርሶ አደሮች ገለፁ። 

በዞኑ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተፋሰስ ልማት ስራ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የለማ ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብልና በፍራፍሬ እየተሸፈነ መሆኑን ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው መልሰው እንዲያገግሙ በተደረጉ አካባቢዎች እያከናወኑ ባሉት የልማት ስራ ተጠቃሚ ሆነዋል። 

በተፋሰስ ልማቱ በለሙ አካባቢዎች ድንች በመትከል ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል በወረዳው የአምበሊ ቀበሌ ነዋሪው መልስ ሟነንዳ ስራው የአፈር ለምነት እንዲመለስ በማድረጉ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።


 

ከዚህ ቀደም ትኩረት ባለመስጠታቸው ለጉዳት ተጋልጦ የነበረው አካባቢ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሰራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አገግሞ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እየሰጠን ይገኛል ብለዋል።

ሌላኛዋ አርሶ አደር ዘምዘም አህመዲን በቀበሌው ከዚህ ቀደም በተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተጎዱ መሬቶች እያገገሙ መሆኑንና አፈር እንዳይሸረሸር ማድረጉን ተናግረዋል። 

ለምነቱ በተመለሰው ቦታ ላይም የተለያዩ ሰብሎችና የመኖ ተክሎችን በማልማት የበለጠ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ለምነቱ በተመለሰው መሬት ላይ እንሰትና ድንች በመትከል በተፋሰስ በለማው መሬት ላይ ደግሞ የገብስ ምርጥ ዘር ለመዝራት መዘጋጀታቸውን የገለፁት ደግሞ በወረዳው የኰኴራ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ዘራብዛ ግርማ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም የቤተሰብ ቀለብ በአግባቡ ከመቻል አልፈው ለገበያ ጭምር ለማምረት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በዞኑ በተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የለሙ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ በሰብልና ፍራፍሬ ተክሎች እየተሸፈኑ ነው።


 

አካባቢዎቹ ከዚህ ቀደም ገላጣና ለም አፈራቸው ተሸርሽረው ከአገልግሎት ውጪ ሆነው የቆዩ ቢሆንም በማህበረሰብ ተሳትፎ በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አገግመው በሰብሎችና ፍራፍሬዎች መሸፈናቸውን አመልክተዋል።

በዚህም በዞኑ በተፋሰስ ስራ የለማ ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶችና ፍራፍሬዎች ከመሸፈናቸውም በላይ ለመኖና ለንብ እርባታ ልማት እንዲውሉ መደረጉን ተናግረዋል።

በወረዳቸው የአፈር ለምነትን የሚጨምሩ የእርከን ስራዎች፣ ውሃ የማቀብና የመከለል ስራ በማከናወን ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በድንች፣ በፍራፍሬና በቅመማ ቅመም መሸፈኑን የተናገሩት ደግሞ የእዣ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መቻል ተሰማ ናቸው።


 

በተጨማሪም የንብ እርባታ እና የተለያዩ የመኖ ሰብሎች እየለሙ መሆኑን አክለው 34 ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም  በዚሁ ልማት አዳዲስ የስራ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም አስረድተዋል።

 

   

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም