የስነ-ምድር አፈጣጠርን የሚያሳዩ አካባቢዎችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የስነ-ምድር አፈጣጠርን የሚያሳዩ አካባቢዎችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማዋል ይገባል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 10/2017(ኢዜአ)፡-ህብረተሰቡ የስነ-ምድር አፈጣጠርን የሚያሳዩ አካባቢዎችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚገባ በአዲስ አበባ እና ቦትስዋና ዩኒቨርሲቲዎች የስነ-ምድር መምህር አስፋውወሰን አስራት (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ በዪኔስኮ ብዝሃ ሃብት ካስመዘገቡት ሀገራት አንዷ ስትሆን በርካታ የሚዳሰሱ፣ የማይዳሰሱ እና ጥብቅ ባዪስፌር ሀብቶች በዩኔስኮ እውቅና ተሰጥቷቸው የተመዘገቡ ናቸው።
መንግስት ከለውጡ ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ከኢኮኖሚ ምሰሶ መካከል አንዱ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን አዲሱ ረቂቅ የቱሪዝም ፖሊሲ የጂኦቅርስ ቦታዎችን መጠበቅ፣ ጂኦፓርኮችን ማቋቋም እና ለጂኦቱሪዝም አስፈላጊነት ትኩረት ሰጥቷል።
በዚህም ኢትዮጵያ በጂኦቱሪዝም በርካታ ሃብቶች ያላት ሀገር ስትሆን የሶፈኡመር ዋሻ፣ ገርአልታ፣ ኮንሶ፣ አፋር፣ ባሌ ተራሮችና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች ተጠቃሽ ናቸው።
በአዲስ አበባ እና ቦትስዋና ዩኒቨርሲቲዎች የስነምድር መምህር አስፋውወሰን አስራት (ፕ/ር) በኢትዮጵያና በአጠቃላይ ምስራቅ አፍሪካ ለስነ-ምድር አፈጣጠር ምርምር የሚሆኑ በርካታ ስፍራዎች ያሉባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
እነዚህ የላቀ ሁለንተናዊ እሴት ያላቸው ስፍራዎች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በጂኦፓርከነት ተመዝግበው ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
እስካሁን 229 ጂኦፓርኮች ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፥ በአፍሪካ የተመዘገቡት ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ታንዛኒያ እና ሞሮኮ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ አፈጣጠርን በአጭር ቦታ የሚያሳዩ የተፈጥሮ አቀማመጦች መኖራቸውን አንስተው፤ ስፍራዎቹ የዓለም ቅርስ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ እነዚህን የስነ-ምድር አፈጣጠርን የሚያሳዩ አካባቢዎችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ተገልጠው የሚታዩ ተራራዎች የሚያመለክቱት በርካታ ታሪክ መኖሩን ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፥ ኢትዮጵያ ለዚህ ዘርፍ እምቅ ጸጋ ያላት ሀገር መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
በጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት እና ፋይዳዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ቀጣናዊ ወርክሾፕ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።
የስልጠናው ተሳታፊ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች በኦሮሚያና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የተመረጡ የጂኦሎጂ እና የአርኪኦሎጂ ቦታዎች ላይ የመስክ ጉብኝት ማድረጋቸውም እንዲሁ።