የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ሰኔ አጋማሽ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ሰኔ አጋማሽ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 10/2017(ኢዜአ)፡-የ2018 ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰኔ አጋማሽ መጀመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ አብይ ኃይለመለኮት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመላ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በርካታ ወጣቶችን በማሳተፍ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች በስፋት ተከናውነዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰኔ አጋማሽ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
ለዚህ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም 14 ዘርፎች መለየታቸውን ጠቁመው፥ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመመዝገብ ስልጠና የመስጠት ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ለሀገር ልማት እና ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተቋማት የበጎ ፍቃድ ስራዎችን የስራቸው አካል አድርገው በመስራት ውጤታማ ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ዜጎች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወነ የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ23 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ57 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በበጎ ፍቃድ ስራው የቤት እድሳት፣የማእድ ማጋራት፣የአረንጓዴ አሻራ፣የሃብት ማሰባሰብና ሌሎችም በርካታ ተግባራት ባለፉት የለውጥ አመታት መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡