144ኛው የኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ በክሪስታል ፓላስ እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
144ኛው የኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ በክሪስታል ፓላስ እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2017(ኢዜአ)፡- የ2024/25 የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ በክሪስታል ፓላስ እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ይደረጋል።
የክለቦቹ ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ 90 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ዌምብሌይ ስታዲየም ይካሄዳል።
ክሪስታል ፓላስ ኤፍኤ ካፕን ለመጀመሩያ ጊዜ ለማንሳት፣ ማንችስተር ሲቲ ደግሞ ለስምንተኛ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ለመሆን ይፋለማሉ።
በግማሽ ፍጻሜው ክሪስታል ፓላስ አስቶንቪላን 3 ለ 0፣ ማንችስተር ሲቲ ኖቲንግሃም ፎረስትን 2 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜው ደርሰዋል።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በኤፍኤ ካፕ ውድድር ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ማንችስተር ሲቲ ሶስቱንም በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
ክሪስታል ፓላስ እ.አ.አ 1990 እና 2016 ለኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ደርሶ በሁለቱም አጋጣሚ በማንችስተር ዩናይትድ ተሸንፏል።
ፓላስ በሶስተኛ የፍጻሜ ጨዋታው ከሌላኛው የማንችስተር ከተማ ክለብ ማንችስተር ሲቲ ጋር ተገናኝቷል።
ማንችስተር ሲቲ ለኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ሲደርስ የአሁኑ ለ14ኛ ጊዜ ነው።
ክሪስታል ፓላስ በ125 ታሪኩ የመጀመሪያ ትልቅ የሚባል ዋንጫውን ለማንሳት እና ታሪክ ለመጻፍ ከፊቱ የቆመውን ማንችስተር ሲቲ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ቡድኑ ካሸነፈ ከዋንጫ ባለፈ በቀጣዩ ዓመት በዩሮፓ ሊግ መሳተፉን ያረጋግጣል።
ማንችስተር ሲቲ የዛሬው ጨዋታ በፔፕ ጋርዲዮላ የአሰልጣኝ ዘመን መጥፎ የተባበለትን የውድድር ዓመት በዋንጫ ለመደምደም የሚፈልግበት ፍልሚያ ነው።
የ42 ዓመቱ ስቲዋርት አትዌል የፍጻሜውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
154 ዓመት ያስቆጠረው ኤፍኤ ካፕ የዓለማችን አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር ነው።