ቀጥታ፡

የማህበረሰቡን የሰላምና የልማት እሴቶች ለማጎልበት ምሁራን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል

ነቀምቴ፤ ግንቦት 9/2017(ኢዜአ)፡- የማህበረሰቡን የሰላምና የልማት አሴቶችና ባህል ለማጎልበት ምሁራን የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተመለከተ።

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ችግሮችን መቋቋም የሚችል ማሕበረሰባዊ ስርዓት ግንባታ ከቋንቋ፣ ከባህል፣ ከሰላም እና ከልማት አንጻር ያተኮረ ዓመታዊ የጥናት እና ምርምር ኮንፍረንስ ተካሂዷል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ለማ(ዶ/ር) እንደተናገሩት ለሁለት ቀናት በተካሄደው ሀገር አቀፍ የጥናት ኮንፍረንስ 31 የጥናትና ምርምር ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የጥናትና ምርምር ኮንፍረንሱ ዋና ዓላማ በዚህ ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ውስጥ ለችግሮች የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባት የሚያግዙ ምክረ ሀሳቦችን ማቅረብ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዋናነት የማህበረሰቡን አሴቶችና ባህል ማዳበርና ማጎልበት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ምሁራንና የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ጠንካራ ከሚባሉ ማህበረሰባዊ እሴቶች መካከል የገዳ ስርዓት አንዱ መሆኑን አንስተው የገዳ ስርዓት የተሻለ የአስተዳደራ ሁኔታ እንዲኖር የሚያግዝ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በሁሉም አካባቢዎች በጎ ማህበራሰባዊ እሴቶችን በማልማትና በማበልጸግ ለወቅታዊ ችግሮች የማይበገር ማህበረሰብ መገንባት እንደሚገባም አስረድተዋል።

በኮንፍረንሱ በተጋባዠ እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ችግሮችን መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚሁ የሚያግዝ የሀገራዊ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ ምክክሩ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሔዎች እንዲያገኙ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ምክክሩ የሁሉንም አካላት ጥረት እንደሚጠይቅና በተለይ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የምሁራን ተሳትፎ እንዲጎለብት ጠይቀዋል።

በኮንፍረንሱ ጥናት ካቀረቡት መካከል በዩኒቨርሲቲው ጊምቢ ካምፓስ የቋንቋ እና ባህል ትምህርት ክፍል መምህር ተመስገን ሶሬሳ(ዶ/ር) ለችግር የማይበገር ማህበረሰብ መገንባት እጽንኦት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለዚህ ደግሞ የሕዝቡን መልካም እሴቶች ማልማትና ማሳደግ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቅሰው፤ በጥናትና ምርምር ኮንፍረንሱም ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን ጠቁመዋል።

በጥናት እና ምርምር ኮንፍረንሱ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም