ቀጥታ፡

የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የተገልጋዮችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት እየሰጠ ነው

አዳማ፤ግንቦት 8/2017 (ኢዜአ)፦የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የተገልጋዮችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የተሟላ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ታካሚዎች ተናገሩ።

የኢትየጵያ ዜና አገልግሎት በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከታካሚዎችና ሃኪሞች ጋር ቆይታ አድርጓል ።

በአዳማ ከተማ ድሬ ነገያ ወረዳ ነዋሪ አቶ በላይነህ ይዘንጋው የሆስፒታሉ ተከታታይ ታካሚ መሆናቸውን ጠቅሰው ዛሬም ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት የተሟላ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

"በሆስፒታሉ እንደወትሮው ሁሉ በሀኪሞችና ባለሙያዎች መልካም አቀባበልና መስተንግዶ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎች የገቡትን ቃል ኪዳን በማክበር እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ሌላው በሆስፒታሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው አቶ በቀለ መኮንን በበኩላቸው "ሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጡን እያሻሻለ በመምጣቱ ዛሬም እንደ ወትሮው የተሟላ ህክምና አግኝቻለሁ" ብለዋል።

"በሆስፒታሉ ከህሙማን መብዛት በስተቀር አገልግሎቱ መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ተገልጋዮች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሆስፒታሉ ጠቅላላ ሀኪም ዶክተር ጽዮን ጌታሁን ናቸው።

በዚህም ተገልጋዮችን የሚያረካ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

አሁን ላይም የገባነውን ቃል ኪዳን በማክበር ለህብረተሰባችን ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን" ብለዋል።

የሆስፒታሉ የተመላላሽ ህክምና ዳይሬክተር ዶክተር ሹሙዝ አህመዩ በበኩላቸው "በአገልግሎታችን ለተገልጋዮች ትኩረት መስጠትና ለስራችን ኃላፊነት መውሰድ ይገባል "ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"በተለይ የምንሰጠው የህክምና አገልግሎት የቡድን ስራ በመሆኑ ከባለሙያ ጋር በመሆን በስራ ክፍላችን በጥልቅ የስራ ዲስፕሊን ተግባራችንን እየከወንን ነው " ብለዋል።

የሙያውን ዲስፒሊን አክብረው በሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥን አጠናክረው ማስቀጠላቸውን አስታውቀዋል።

በሆስፒታሉ የነርሶች አስተባባሪ ሲስተር ዓለምጸሀይ ወጋሳ "የሆስፒታሉን ህክምና አገልግሎት ፍለጋ በርካታ ህሙማን ከሩቅ አካባቢ ጭምር የሚመጡ በመሆኑ የሆስፒታሉ መደበኛ አገልግሎት ተጠናክሮ ቀጥሏል" ብለዋል።

የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ሥራ እስኪያጅ ዶክተር ስንታየሁ ተክሌ እንዳሉት ሆስፒታሉ ለማህበረሰቡ የተሟላ ህክምና መሰጠትን እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ደግሞ ብቁ የሆነ ከፍተኛ ሀኪሞችን ለማፍራት አላማ አንግቦ እየሰራ ይገኛል።

"በተለይም ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ማእከል ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀት በመዘርጋት የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።

ሆስፒታሉ በዓመት በተመላላሽ ህከምና ለ330 ሺህ ህሙማን እንዲሁም ፣ በቀዶ ጥገና ለ10 ሺህ ህሙማንና ለ10 ሺህ ነፍሰ ጡር አናቶችም የማዋለድ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት በማሻሻል ተገልጋይ ተኮር ለማድረግ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም