ኢትዮጵያ ለጂኦፓርክ እና ጂኦቱሪዝም የሚሆኑ እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎች እንዳሏት ለመገንዘብ ችለናል -ጎብኝዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለጂኦፓርክ እና ጂኦቱሪዝም የሚሆኑ እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎች እንዳሏት ለመገንዘብ ችለናል -ጎብኝዎች
አዲስ አበባ፤ግንቦት 8/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለጂኦፓርክ እና ጂኦቱሪዝም የሚሆኑ እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎች እንዳሏት መገንዘብ መቻላቸውን ጎብኝዎች ገለጹ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ጋር በመተባበር "የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ለዓለም አቀፍ የዘርፉ ምሁራን ከግንቦት 4 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።
ስልጠናውን ተከትሎ የፌዴራል ተቋማት ሀላፊዎች፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን እና ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የዩኔስኮ ባለሙያዎች የተመረጡ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጎብኝተዋል።
የጢያ ትክል ድንጋይ እና የመልካ ቁንጡሬ ባልጪት የአርኪዮሎጂ ስፍራ እና በአካባቢው የሚገኙ የጂኦሎጂ ቅርሶችን እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ የጂኦሎጂ ስፍራዎች ከተጎበኙት መካከል ናቸው ።
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የተፈጥሮ ሳይንስ ፕሮግራም ስፔሻሊስት የሆኑት ኦዝለም አዲያማን ሎፔዝ (ዶ/ር) በጉብኝታቸው የሚያስደንቅ ቦታዎችን ማየታቸውን ገልጸዋል።
የተመለከቱት ድንጋዮች አስደናቂና ታሪክን የሚናገሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤የአካባቢው ህብረተሰብም እነዚህን ድንጋዮች እየጠበቀ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ጂኦፓርክ የተባለውን የዩኔስኮ አዲስ ጽንሰ ሀሳብ ለማስተዋወቅ በኢትዮጵያ መገኘታቸውን ገልጸው፥ እነዚህ ድንጋዮች እንዴት እንደተፈጠሩ፣ከየት እንደመጡ እና ይህ ስፍራ ከማህበረሰቡ ጋር እንዴት እንደተገናኘ የምናስተዋውቅበት ነው ብለዋል።
ከታንዛኒያ የመጣው ባካሪ ማናያ በበኩሉ፥ የተመለከታቸው አካባቢዎች ለትምህርታዊ አላማዎች እና መነሻችንን ለማወቅ በጣም ጠቃሚ ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ እነዚህን ሀብቶች ጠብቆ ለማቆየት የሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።
ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት በጣም አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የተፈጥሮ ሳይንስ ባለሙያ ሶፊ ጀስትስ ናቸው።
የጂኦሎጂካል ቅርስ ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፥ እነዚህ ቅርሶች በዓለም ዙሪያ አንድ ወይም ሁለት ልዩ ቦታዎች ላይ ብቻ የሚገኙ መሆናቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በተመለከቱት አስደናቂ ስፍራዎች ጂኦፓርክን ለማዳበር የሚደረገውን ጥረት የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሩዋንዳ የመጡት ክሬግ ማኩንዚም ኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃ እንዲሁም በአካባቢው የማህበረሰብ ስለ ቦታው ያለው ግንዛቤ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ለህብረተሰቡ ሆነ ለቱሪስቱም በጣም ጠቃሚ መሆኑን አንስተው፥ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በጂኦ ቱሪዝም በርካታ ሃብቶች ያላት ሲሆን፤ ሶፍ-ዑመር፣ ገርአልታ፣ ኮንሶ፣ አፋር፣ ባሌ ተራሮችና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርኮችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
የስነ ምድር አፈጣጠርን የሚያሳዩ ስፍራዎችን በዓለም አቀፍ መዝገብ በጂኦ ፓርክነት ለማስመዝገብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል።