የኢትዮጵያን ባንኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ምቹ መደላድል እየተፈጠረ ነው -የባንክ የስራ ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ባንኮች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ምቹ መደላድል እየተፈጠረ ነው -የባንክ የስራ ኃላፊዎች
አዲስ አበባ፤ግንቦት 8/2017(ኢዜአ)፦በኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ባንኮች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተወዳዳሪነት አቅም ለማሳደግ ምቹ መደላድል እየተፈጠረ እንደሚገኝ የባንክ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም በሳይንስ ሙዚየም ዛሬም ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ሲሆን፥ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎታቸውን የሚያሳዩበት አውደርዕይ ተከፍቷል።
በዘመን ባንክ የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ግሩም ታሪኩ፥ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን ዕድገት በማሳለጥ ለባንክ ኢንዱስትሪው አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓቱ ገበያ መር መደረጉም በሕገ-ወጥ መንገድ በትይዩ ገበያ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ገንዘብ ወደሕጋዊ የፋይናንስ ተቋማት እንዲመጣ እያደረገ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ባንኮች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ያላቸው በመሆኑ ለደንበኞቻቸው የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች መከፈቱ የሀገር ውስጥ ባንኮች ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን እንዲዘጋጁ መነሳሳትን መፍጠሩንም አስረድተዋል።
በዚህም በሰው ሀብት ልማት፣በቴክኖሎጂ ግብዓትና አጠቃቀም የተሻለ አቅም እንድንፈጥር እያደረገን ነው ብለዋል።
በኦሮሚያ ኮኦፕሬቲቭ ባንክ የለውጥና ስትራቴጂ ዋና ኦፊሰር አማን ሠሚር፥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲፈጠር እያደረገ ነው ብለዋል።
በባንክ ኢንዱስትሪው ህጋዊ ምህዳርን የተከተለና የተፍታታ የገንዘብ አስተዳደርና እንቅስቃሴ እንዲኖር ማስቻሉን ገልጸዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ እመርታዊ ውጤት እየመጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ለዲጅታል ሽግግር በተሰጠው ትኩረት የባንክ ዘርፉ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለአብነትም የዲጅታል የብድር አገልግሎት ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
በአዋሽ ባንክ የዲጂታል ግብይት ዲቪዥን ማናጀር ይበልጣል አርጋቸው(ዶ/ር)፥የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የባንኮች ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሬ ክምችትን በማሳደግ ደንበኞች እንደየፍላጎታቸው መስተናገድ የሚችሉበትን ዕድል እንደፈጠረም አስረድተዋል።