በወላይታ ሶዶ ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ-ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ-ፖሊስ

ወላይታ ሶዶ፣ግንቦት 8/2017 (ኢዜአ)፦በወላይታ ሶዶ ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የትራፊክ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ ሃላፊ ዋና ሳጅን ዝናቡ ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በከተማው በተለምዶ መናፈሻ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ዛሬ ጠኋት 3 ሰዓት 20 ደቂቃ ላይ ነው፡፡
ከሀዋሳ ወደ ወላይታ ሶዶ ሲጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 04178 ሲዳ የሆነ ዶልፊን አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 24386 ኢት ከሆነ ተሳቢ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።
በአደጋው የአነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪ ጨምሮ በውስጡ የነበሩ የአራት ሰዎች ህይወት ወድያው ማለፉን ተናግረዋል።
የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ለህክምና እርዳታ ወደ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል መላካቸውን ገልጸዋል።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን አስታውቀዋል ።