ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ከፍተኛ አቅም አለ- እመቤት መለሰ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ግንቦት 8/2017(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ከፍተኛ አቅም መኖሩን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በሳይንስ ሙዚየም በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ጉባኤ "የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ፤የቅርብ ጊዜ ዕድገቶች፣የማሻሻያ እርምጃዎችና የቁጥጥር ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፥ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ለኢንቨስትመንት አዋጭ የሆነ ያልተነካ ዕምቅ አቅም አለ ብለዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ የባንክና የገንዘብ ተቋማትም መዋለነዋያቸውን ፈሰስ ቢያደርጉ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ከፍተኛ የገበያ ዕድል መኖሩን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የልማት አቅም የሆነ ወጣትና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ሃብት መኖሩ ኢንዱስትሪውን ለመጠቀም መልካም አጋጣሚ እንደሆነም አስረድተዋል።

የዚህ ዘመን ትውልድ የዲጂታል ባንኪንግ ሥርዓት ይፈልጋል ያሉት የባንኩ ፕሬዝዳንት፥አብዛኞቹ የዓለም አቀፍ ባንኮችም በዲጂታል ባንኪንግ ዕውቀት ያካበቱ ናቸው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ባንኮች የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅማቸውን ተጠቅመው ቢሰሩ በኢትዮጵያ መዋለ ነዋይ በማፍሰስ የገንዘብና የገበያ አቅማቸውን ለማሳደግ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ የባንክና የፋይናንስ ተቋማትም የባንኪንግ ኢንዱስትሪ ገበያ በመጠቀም መዋለ ንዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ትናንት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም የተጀመረው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም