ቀጥታ፡

በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት በቂ ዝግጅት እያደረግን ነው-ተፈታኝ ተማሪዎች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 8/2017(ኢዜአ)፦በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችለንን ቅድመ ዝግጅት እያደረገን ነው ሲሉ ተፈታኝ ተማሪዎች ገለጹ።

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሀምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በመላ ሀገሪቱም ከ600 ሺህ በላይ የተፈጥሮ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናውን በወረቀት እና በበይነ መረብ እንደሚወስዱ የወጣው ፕሮግራም ያሳያል።

ኢዜአ ለሀገር አቀፍ ፈተናው እየተደረጉ ያሉ ቅድመ ዝግጅቶችን አስመልክቶ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች እና የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን አነጋግሯል።

በኮከበ ፅባህ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ አብርሃም ሠላምነህ በብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ወደ አዲስ የትምህርት ምዕራፍ ለመሻገር ሰፋ ያለ ዝግጅት እያደረኩ ነው ብሏል።

በተለይም ለፈተናው የሚረዱትን መጽሀፍት እንዲሁም በበይነ መረብ አማካኝነት አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን በማንበብ ላይ እንደሚገኝ ነው ያብራረው።

ሀገር አቀፍ ፈተናው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የተማርናቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የሚሸፍን በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ የአጠናን ዘዴ በመጠቀም እየተዘጋጀሁ እገኛለሁ ያለችው ደግሞ በዚሁ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ የሆነችው ዳናት ባህሩ ናት።

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አማኑኤል ታሪኩ በበኩሉ፥ ውጤታማ በመሆን ህልሙን እውን ለማድረግ በትምህርቱ ላይ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

ይህንን ጥረት ከግብ ለማድረስም በቀጣይ ወር በሚሰጠው ሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ከዚህ ቀደም የተማራቸውን ትምህርቶች ወደ ኋላ መለስ ብሎ በመከለስ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ሌላኛዋ የካምፓሱ ተማሪ ሰሎሜ ታደሰ በፈተናው ውጤታማ እንድንሆን መምህራኖቻችን ጥያቄዎችን እንድንሰራ በማድረግና በሌሎች በሚያስፈልጉን ነገሮች እየደገፉን ይገኛሉ ብላለች።

ፈተናው እየተቃረበ በመምጣቱ በእውቀትም በስነ-ልቦናም ብቁ ለመሆን ጥረቷን እንደምታጎለብት ገልፃለች።

ተማሪ አማኑኤል በበኩሉ፥ተፈታኞች ራሳቸውን በሚገባው ልክ በማዘጋጀትና በመፈተሽ ለላቀ ውጤት ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

የኮከበ ፅባህ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደለለኝ አስማረ በበኩላቸው፥ ትምህርት ቤቱ በዘንድሮ ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 632 የቀን 63 የማታ ተማሪዎችን ያስፈትናል ብለዋል።

ትምህርት ቤቱም ተፈታኝ ተማሪዎች ለፈተናው በሚፈለገው ደረጃ እንዲዘጋጁ ለማድረግ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲወስዱ እና ተፈታኞች በግቢው እያደሩ ማጥናት የሚችሉበት ሁኔታ ማመቻቸቱን ተናግረዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎቹ በወረቀት እና በበይነ መረብ የሚፈተኑ መሆናቸውን በማንሳት በተለይም በበይነ መረብ ለሚፈተኑ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በኮምፕዩተር ልምምድ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ምክትል ርዕሰ መምህር አብርሃም ድሪባ፥ ካምፓሱ በሀገር አቀፉ የ12ኛ ክፍል ፈተና 80 ተማሪዎችን እንደሚያስፈትን አስታውቀዋል።

ተማሪዎቹም ለረጅም ዓመታት በትምህርት ዓለም ያደረጉት ጉዞ ፍሬያማ እንዲሆን የተለያዩ ሞዴል ፈተናዎችን እየወሰዱ እንደሚገኙ አንስተው፥ ይህም እስከ ፈተናው መዳረሻ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም