የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8 /2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል።
የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሲዳማ ቡና በ40 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም።
ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ያሸነፈው ወላይታ ድቻ በ41 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማሸነፍ ለሁለቱም ቡድኖች ደረጃቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል።
ምሽት 12 ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይጫወታሉ።
ሃዋሳ ከተማ በ34 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አራቱን በማሸነፍ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛል።
የ16 ጊዜ የሊጉ የዋንጫ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ40 ነጥብ 7ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ እንዲመለስ ያደርገዋል።
የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያሉ።
ኢትዮጵያ መድን ሊጉን በ57 ነጥብ እየመራ ነው። ኢትዮጵያ ቡና በ48 ነጥብ ይከተላል።
መቀሌ 70 እንደርታ ፣ አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛሉ።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የሃዋሳ ከተማው ዓሊ ሱሌይማን በ12 ግቦች እየመራ ነው።
የመቻሉ ሽመልስ በቀለ እና የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በተመሳሳይ 11 ጎሎችን በማስቆጠር ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።