ቀጥታ፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማዕከላትን በመደገፍ ተግባራቸውን ማጠናከር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማዕከላትን በመደገፍ ተግባራቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ገለጹ።

ኮርፖሬሽኑ ለሶስት የበጎ አድራጎት ተቋማት የአስር ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

በዚህም ለመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አምስት ሚሊዮን ብር፣ የእንግዳ ማረፊያ ቤትና የንግድ ሱቅ አበርክቷል።

በተጨማሪም ለሲር ለና እና ለእዝነት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለእያንዳንዳቸው የሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር እገዛ አድርጓል።


 

በዚሁ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ረሻድ ከማል እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ በቤትና ኮንስትራክሽን ልማት ዘርፍ ተልዕኮውን ለማሳካት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

ኮርፖሬሽኑ ከተልዕኮው ባሻገር በተለያዩ በጎ አድራጎት ተግባራት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሶስቱ የበጎ አድራጎት ተቋማት የተደረገው ድጋፍ የዚሁ አካል መሆኑን ነው የገለጹት።


 

ለበጎ አድራጎት ስራ የተቋቋሙ ማዕከላትን መደገፍ የሁሉም ዜጋ እና ተቋማት ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው፤ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

የመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢንያም በለጠ፤ ኮርፖሬሽኑ ማዕከሉን በተደጋጋሚ መደገፉን አስታውሰው፤ በተቋሙ የሚደረገው ድጋፍ ማዕከሉን በዘላቂነት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

የሲር ለና በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ድጋፍ የሚሹ እናቶችና ህጻናትን ማገዝ ላይ በማተኮር መቋቋሙን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ሱስ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች ከሱሱ እንዲያገግሙ በማድረግና የሙያ ስልጠና በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ኮርፖሬሽኑ ያደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ በማዕከሉ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚረዳ ተናግረዋል።


 

የእዝነት የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራች ወይዘሮ ዘይባ አህመድ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ለአካል ጉዳተኛ ህጻናት በቋሚነት አስፈላጊው እገዛ በማድረግ እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ኮርፖሬሽኑ ያደረገላቸው ድጋፍ ስራቸውን በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም