የባዮ ጋዝ የኃይል አማራጭን በመጠቀማችን አድካሚ የነበረው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ተቃሏል - ኢዜአ አማርኛ
የባዮ ጋዝ የኃይል አማራጭን በመጠቀማችን አድካሚ የነበረው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ተቃሏል
ደሴ፤ግንቦት 7/2017 (ኢዜአ)፦በደቡብ ወሎ ዞን የባዮ ጋዝ የኃይል አማራጭን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በመጠቀማቸው አድካሚ የነበረው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው መቃለሉን የዞኑ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የዞኑ ውሃና ኢነርጂ መምሪያ በበኩሉ ከ36 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የተለያዩ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች እንደገለፁት፤ የኃይል አማራጮቹ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ቀላል በማድረጋቸውም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በማዋል ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏል።
በዞኑ የወረኢሉ ወረዳ የ08 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አበበች በላይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የባዮጋዝ ተገንብቶላቸው የኃይል አማራጭ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በዚህም ለማገዶ ያወጡት የነበረውን ጉልበትና ጊዜ ከማስቀረቱም ባለፈ በምግብ ማብሰል ወቅት የሚወጣው ጭስ ከሚያደርስባቸው የዓይን ህመም እንደታደጋቸውም አስረድተዋል።
በተጨማሪም የባዮጋዝ ተረፈ ምርትን እንደ ማዳበሪያ በመጠቀም የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
ሌላው የተሁለደሬ ወረዳ የ02 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ ይመር በበኩላቸው በጸሐይ ብርሃን የሚሰራ የመብራት ቴክኖሎጂና የተሻሻለ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዚህም "ስራችን ተቃሏል፣ ድካማችንም ቀንሷል" ያሉት አርሶ አደሩ በተለይ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃው ጊዜና ጉልበት ከመቆጠቡም ባለፈ የማገዶ ፍጆታቸውን እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡
በጸሐይ ብርሃን የሚሰራ አምፖል መጠቀማቸው የኩራዝ ጭስ በጤናቸው ላይ ያደርስ የነበረውን ችግር ከማስቀረቱም በላይ አሁን ካለው የነዳጅ ውድነትና መጥፋት እንደገላገላቸው ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ የአማራጭ ኢነርጂ ልማት ቡድን መሪ አቶ ይርጋለም ደምሴ በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት አስር ወራት ከ36 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የኃይል አማራጮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮቹን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለውም 311 የባዮጋዝ መጠቀሚያዎችን በማስገንባት፣ 30 ሺህ 865 የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችና 5 ሺህ 215 የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት እንደሆነም ጠቁመዋል።
አማራጭ የኃይል ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ጊዜና ጉልበቱን ለሌሎች የልማት ስራዎች በማዋል ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ የደን ጭፍጨፋን አስቀርቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ባዮ ጋዝ ገንብተው የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ተረፈ ምርቱን እንደ ማዳበሪያ በመጠቀም ከዘመናዊ ማዳበሪያና ኮምፖስት የተሻለ ምርት ማግኘት መቻላቸውን አስረድተዋል።
በዞኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከ35 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የተለያየ ኃይል አማራጭ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሎ እንደነበር ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።