ቀጥታ፡

ቅርሶች የሀገራዊ ገፅታ ግንባታ እና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል

ጂንካ፤ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ቅርሶችን ከታሪካዊ አሻራነታቸው ባለፈ የሀገራዊ ገፅታ ግንባታና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ አመለከቱ።

የአፍሪካ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ቀን በጂንካ ከተማ ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ወይዘሮ ሕይወት እንደገለፁት፥በአገራችን የሚገኙ ባህላዊ፣ታሪካዊ እና የተፈጥሮ ቅርሶች ከታሪካዊ አሻራነታቸው ባሻገር የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለአለም ህዝብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው።

በሀገራችን ያሉ ቅርሶች የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡና በሌሎች ዓለም አገራት የማይገኙ ድንቅዬና ብርቅዬ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ይህን ዕድል መጠቀም ይገባል ብለዋል።

በክብረ በአሉ ላይ የታደሙ የዘርፉ የመንግስት ኃላፊዎችም በአካባቢያቸው ያሉ የቱሪዝም ፀጋዎችን በማልማት ለገፅታ ግንባታና ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት እንዲውሉ እየሰሩ እንዳሉ ተናግረዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኮንሶ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰራዊት ዲባባ፥ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የኮንሶ መልክዓ ምድርን ጨምሮ በዞኑ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

እነዚህ ሀብቶችን በማልማት ለጎብኚዎች ተመራጭ እንዲሆኑ መምሪያው እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፥ በተሰራው ስራም የገቢ ምንጭ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በዩኔስኮ የተመዘገበው የታችኛው ኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስን ጨምሮ በዞኑ 11 ብርቅዬና ድንቅዬ ቅርሶች አሉን ያሉት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ካይ ኢትልቦንግ ናቸው።

እነዚህን ሀብቶች የመጠበቅ፣የመንከባከብና የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው፥ ቅርሶቹ የገቢ ምንጭ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያመጡ ናቸው ብለዋል።

በአፍሪካ ለ9ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ3ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የአፍሪካ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ቀን "ቅርሶች ለማህበራዊ ትስስርና ለማህበረሰብ ጥቅም'' በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ከተማ በአውደ ርዕይ እና በሌሎች መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም