ቀጥታ፡

መንግስት ቱሪዝምን የዓለም አቀፍ ትብብር አማራጭ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወነ ነው-ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦መንግስት ቱሪዝም የዓለም አቀፍ ትብብር አማራጭ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያን ቱሪዝም የሚያስተዋውቅ “Africa Travel Show Media Event” የተሰኘ ሁነት በለንደን ተካሄዷል።

በሁነቱ ላይ ተቀማጭነታቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉ ከ40 በላይ ጋዜጠኞች፣የጉዞ ፀሐፊዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና አፍሪካ ትራቭል ኮኔክት የተሰኘ ዓለም አቀፍ ማህበር ፕሮግራሙን በጋራ አዘጋጅተውታል።

በዝግጅቱ የኢትዮጵያ ብዝሃ የቱሪዝም ሀብቶች ተዋውቀዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢትዮጵያ የቅርስ ስፍራዎች፣መልክዓ ምድሮች እና የባህል ልማዶች ከዜጎች የዕለት ተዕለት ህይወት ጋር የቀጥታ ግንኙነት ያላቸው እና ለዘላቂ ቱሪዝም ልማት ቁልፍ ምሰሶዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የቱሪዝም ዘርፉ የኢኮኖሚ እድገት የለውጥ ሞተር እና የዓለም አቀፍ ትብብር አማራጭ እንዲሆን ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዝግጅቱ ላይ ከኬንያ፣ጋና፣ ሩዋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ የተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣናዊ የትብብር መንፈስ የአፍሪካ የቱሪዝም ሀብት በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የሁነቱ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም እንደሳባቸው እና ዘርፉን ለማስተዋወቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ በዓለም የጉዞ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላት እንደሆነ ተገልጿል።

የሚዲያ ሁነቱ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና አፍሪካ ትራቭል ኮኔክት እ.አ.አ አፕሪል 2025 የተፈራረሙት የጋራ መግባቢያ ሰነድ አካል ነው።

ስምምነቱ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ስትራቴጂካዊ የሚዲያ ትስስር እና ዓለም አቀፍ ትብብሮች ለማስተዋወቅ መሰረት መጣሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም