ቀጥታ፡

ጉብኝቱ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የሚነዙ የሃሰት መረጃዎችን ማጋለጥ የሚያስችል ውጤታማ ተግባር ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ተቋማት ስብሰባ ተሳታፊዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያደረጉት ጉብኝት ግድቡን አስመልክቶ የሚነዙ የሃሰት መረጃዎችን ማጋለጥ የሚያስችል ውጤታማ ተግባር መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ታዜር ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።

ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ታዜር ገብረእግዚአብሔር ዛሬ በሰጡት መግለጫ "በመረጃ ትብብር የቀጣናውን ደኅንነት ማጠናከር" በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ተቋማት ስብሰባ በስኬት ተጠናቋል።


 

ስብሰባው መጠናቀቁን ተከትሎ የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ተቋማት ተሳታፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡

የግድቡ ግንበታ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በመድረሱ የስብሰባው ተሳታፊዎች እንዲያዩት መደረጉን ነው ያመለከቱት።

ጉብኝቱ ሁለት ዓላማዎች እንደነበሩት ያነሱት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ፤ ይህም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች አፍሪካ ሀገራትም ከተባበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መገንባትም ሆነ መፈጸም እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መጎብኘታቸው በግድቡ ዙሪያ የሚነዙ የሃሰት መረጃዎችን ለማጥራት እና ሌላው ማህበረሰብ እውነታውን እንዲረዳ ለማድረግ ያስቻለ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።


 

ተሳታፊዎችም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በጁባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም፣ ልማት እና ጸጥታ ጥናት ተቋም ረዳት ፕሮፌሰር ቴር ቶንጊክ ማጆክ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከጎበኙት መካከል ናቸው፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ቴር ቶንጊክ ማጆክ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከቀጣናዊ ትብብር አኳያ ትልቅ ፋይዳ አለው።

ይህ ታላቅ ስራ በመሆኑም ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን መመልከታቸውንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም